ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው እና አቶ ተስፋዬ  ንዋይ ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት መጻሕፍት አበረከቱ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው እና አቶ ተስፋዬ ንዋይ ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት 350 መፅሐፍትን  አበረክተዋል።

መፅሐፍቶቹን የአብርሆት ቤተ መፅሐፍ ዳይሬክተር ኢንጂነር ውብአየሁ ማሞ ተረክበዋል።

በመከላከያ ህብረት ዘመቻ ዋና መምሪያ የኃይል ሥምሪትና ክትትል መምሪያ ኃላፊ ሜጀር ጄነራል ተስፋዬ አያሌው በቅርቡ "የጀግንነት ሥነ ልቦና" በሚል ርዕስ ለንባብ ያበቁትን መፅሐፍ ለአብርሆት ቤተ መፅሐፍት አስረክበዋል፡፡


 

መፅሐፍቱ በቁጥር 200 ሲሆኑ በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ፣ በሶማሌኛ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ናቸው።

ትውልዱ ይህንኑ መፅሐፍት በማንበብና የጀግንነት ስነ ልቦና በመላበስ ለሀገሩ ሁለንተናዊ ስኬት የበኩሉን እንዲወጣ ያግዛል ብለዋል።

ተማሪዎች የክረምት ጊዜያቸውን በአብርሆት ቤተ መፅሐፍት በማሳለፍ የንባብ ባህላቸውን እንዲያዳብሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተስፋዬ ንዋይ በበኩላቸው በራሳቸው የተፃፉ የፍትህ ጉዳይ፣ የመሬት ሕግ እና አተገባበርን ጨምሮ የአመራር ክህሎት ርዕስ ያላቸውን 150 መፅሐፍትን ለአብርሆት ቤተ መፃሕፍት ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

ዛሬ ያበረከቷቸውና ከዚህ ቀደም ለቤተ መፅሐፍቱ የሰጧቸው መፅሐፍቶች በአብርሆት በኩል ለበርካታ አንባቢያን ተደራሽ መሆን እንደሚችሉ ገልጸዋል።

ዛሬ ለአብርሆት ቤተ መጽሃፍት የተበረከቱት መፅሐፍቶች በፍትህ ጉዳይ፣ በመሬት ሕግ እና አተገባበርን ጨምሮ በአመራር ክህሎት እውቅት የሚያስጨብጡ ናቸው ብለዋል።

የአብርሆት ቤተ መፅሕፍት ዳይሬክተር ኢንጂነር ውብአየሁ ማሞ የተበረከቱት መፅሐፍቶች ትውልድን በጀግንነት፣ በፍትህና በአመራርነት ክህሎት በመገንባት ረገድ ከፍተኛ አበርክቶ አላቸው ብለዋል።

ለተደረገው ድጋፍ በማመስገን ሌሎች አካላትም ለቤተ መፅሐፍቱ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

 

 

 

 


 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም