በተለያዩ የትብብር መስኮች ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያና የአልጄሪያ ግንኙነት ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በተለያዩ የትብብር መስኮች ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያና የአልጄሪያ ግንኙነት ተጠናክሮ ቀጥሏል
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ በተለያዩ የትብብር መስኮች ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያና የአልጄሪያ የሁለትዮሽ ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠሉን በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር ሞሃመድ ላሚን ላባስ ገለጹ።
አምባሳደር ሞሃመድ ላሚን ላባስ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያና አልጄሪያ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀና በተለያዩ የትብብር መስኮች ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ወዳጅነት አላቸው።
የሁለቱ አገራት ግንኙነት የተጀመረው፤ አልጄሪያ ከቅኝ ግዛት ለመላቀቅ በምታደርገው የነጻነት ትግል ኢትዮጵያ ከጎኗ መቆሟን ተከትሎ መሆኑን አንስተው ይህም ግንኘነቱን ታሪካዊ ያደርገዋል ነው ያሉት።
ከዚህም በኋላ ሁለቱ አገራት በተለያዩ ጊዜያት በሚገጥማቸው ፖለቲካዊ ችግሮች እርስ በእርስ በመደጋገፍና መፍትሄ በማፈላለግ ያላቸውን ታሪካዊ አጋርነት ይበልጥ እየተጠናከረ መምጣቱንም አብራርተዋል።
በባህል እንዲሁም በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መስክም አጋርነቱ እየተጠናከረ መምጣቱን አንስተው ፤ለዚህም በርካታ የኢትዮጵያ ተማሪዎች በአልጄሪያ ትምህርታቸውን መከታተል መቻላቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በምጣኔ ኃብት ዘርፍ በተለይም በንግድና ኢንቨስትመንት የሁለቱ አገራት ግንኙነትን ለማጠናከር የሚያስችል የጋራ ሥልት ተቀይሶ ወደ ሥራ መግባቱን ጠቁመው፤ በዚህም የአገራቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የጉብኝት ልውውጥ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በቅርቡም በፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ላይ የተሰማሩ ልዑካን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የኢንቨስትመንት አማራጮችን መመልከት መቻላቸውንና መሰል እንቅስቃሴዎች በቀጣይ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በተለይም በግብርና ዘርፍ የሁለቱን አገራት የኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በንግዱ ዘርፍ፤ አልጄሪያ ከፍተኛ የቡና ተጠቃሚ አገር መሆኗን ጠቅሰው፤ ከኢትዮጵያ ቡናን በስፋት ወደ አልጄሪያ ለማስገባት እንዲሁም አልጄሪያን የኢትዮጵያን የአበባ ምርት ተጠቃሚ ለማድረግ የአየር ትራንስፖርቱን በማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የአየር ትራንስፖርት ሲጠናከር የአልጄሪያ ምርቶች በኢትዮጵያ፤ በአንጻሩ የኢትዮጵያ ምርቶች በአልጄሪያ እናያለን ብለን ተስፋ እንደርጋለን ብለዋል።
ኢትዮጵያና አልጄሪያ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ ተደራራቢ ታክስን በማስቀረትና በሌሎች የትብብር መስኮች ከ20 በላይ ሥምምነት ከዚህ ቀደም አድርገዋል።
የእነዚህን ሥምምነቶች ትግበራ ለማቀላጠፍ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል ያሉት አምባሳደሩ፤ በሁለቱ አገራት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ደረጃ የፖለቲካ ምክክሮችና ውይይቶች ተጠናክረው መቀጠላቸውን አንስተዋል።
በዚህ ረገድ የሁለቱ አገራት የጋራ ኮሚሽን የተሰሩ ሥራዎችን በመገምገምና ቀጣይ አቅጣጫ በማስቀመጥ ረገድ ትልቅ ሚና እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያና አልጄሪያ የጋራ በሆኑ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ለአብነትም በሰላምና ደኅንነት በተለይም ሽብርተኝነትን በመወጋትና እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል የጋራ አቋም እንዳላቸው ጠቅሰው፤ ለዚህም በጋራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተለይም የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ችግኞችን በመትከል እየሰራች ያለው ሥራ የሚበረታታና ይህም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች አገራትም ጭምር ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ አንጻር፤ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ታች ወርደው ችግኝ በመትከል የሚያሳዩት አርአያነት ያለው ተግባር የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
አምባሳደር ሞሃመድ ላሚን ላባስ ከ40 ዓመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንደነበር ጠቅሰው ኢትዮጵያ አሁን ላይ ያለችበት የእድገት ደረጃ የሚደነቅ መሆኑንም አንስተዋል።
የአልጄሪያና የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጠጣር በ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።