ኢሉ አባቦርን ዞንን ከቱሪዝም ሀብቱ ተጠቃሚ ለማድረግ መስኅቦችን የማልማትና የማስተዋወቅ ስራ በትኩረት እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢሉ አባቦርን ዞንን ከቱሪዝም ሀብቱ ተጠቃሚ ለማድረግ መስኅቦችን የማልማትና የማስተዋወቅ ስራ በትኩረት እየተከናወነ ነው

መቱ ፤ ሐምሌ 19/2016 (ኢዜአ)፡- ኢሉ አባቦርን ዞንን ከቱሪዝም ሀብቱ ተጠቃሚ ለማድረግ መስኅቦችን የማልማትና የማስተዋወቅ ስራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ገለጸ።
በዞኑ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ እና ባሕላዊ መስኅቦችን ለማስተዋወቅ በተሰሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መመዝገባቸው የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ወንድሙ ደበላ ለኢዜአ አስታውቀዋል።
በዚህም በዞኑ የሚገኙ መስኅቦችን በመለየት በተሰራው የሚስተዋወቅ ስራ በርካታ ሰዎች የሶር ፏፏቴ መጎብኘታቸውን ገልጸዋል።
በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የዓለም ቱሪዝም ቀን በስፍራው እንዲከበር በማድረግም ተጨማሪ የማስተዋወቅ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ አስጎብኚዎች ማኅበር አባላትን ጨምሮ ሌሎች በቱሪዝም ዙሪያ የሚሰሩ አካላትን ወደ ዞኑ በማምጣት መስኅቦቹን እንዲጎበኙ መደረጉንም ተናግረዋል።
በዚህም በዓመቱ ወደ ዞኑ የመጡ እንግዶችና የመንግሥት አካላት ሶር ፏፏቴን ጨምሮ የተለያዩ መስህቦችን መጎብኘታቸውን ገልጸዋል።
በዞኑ በበጀት ዓመቱ ከዘርፉ የተሻለ ገቢ መገኘቱን የተናገሩት ኃላፊው፣ መስህቦቹን በማልማትና በማስተዋወቅ የዞኑን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን መስኅቦቹን በማልማቱ በኩል በተሰሩት ስራዎች በዞኑ በቾ ወረዳ ወደ ሶር ፏፏቴ የሚወስድ 5 ኪሎ ሜትር፣ በአሌ ወረዳ ወደሚገኝ ታሪካዊ ስፍራ የሚወስድ 17 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገዶች መሰራታቸውን ገልጸዋል።
በዞኑ ባለፈው ዓመት የተቋቋመው ፓርክም የተለያዩ የዱር እንስሳት ዝርያዎች፣ አዕዋፋት፣ መልክዓ ምድርና የደን ዛፎች ዝርያዎች ያሉበት ሲሆን፣ በዞኑ የቱሪዝም ሀብት ላይ ተጨማሪ አቅም መሆኑን ገልጸዋል።
በዞኑ የሶር ፏፏቴን ጨምሮ ሌሎች ተፈጥሯዊ መስህቦች ከሚገኙባቸው ወረዳዎች አንዱ በሆነው የበቾ ወረዳ መስህቦቹን ማልማት ስራ እይተከናወነ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የወረዳው ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተመስገን ወንድሙ ናቸው።
በተለይም ሶር ፏፏቴን ለሚጎበኙ ቱሪስቶች በአግባቡ ለማስተናገድ የሚያግዝ የእንግዳ መቀበያ መገንባቱን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የሶር ፏፏቴን በመጠበቅና በማስተዋወቅ ስራ ላይ ወጣቶችን በአስጎብኚነት ጭምር በማደራጀት የስራ ዕድል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን አቶ ተመስገን አስታውቀዋል።