ግዙፉ የስፖርት ሁነት የፓሪስ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
ግዙፉ የስፖርት ሁነት የፓሪስ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ በፓሪስ የሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ዛሬ በይፋ ይጀመራል።
የዘንድሮው ኦሊምፒክ መክፈቻ በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከስታዲየም ውጪ በወንዝ ላይ ይደረጋል።
በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከ203 ሀገራት የተወጣጡ 10 ሺህ 500 አትሌቶች በ32 የስፖርት አይነቶች እንደሚወዳደሩ የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መረጃ ያመለክታል።
ከሀገራቱ በተጨማሪ በዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጥላ ስር ገለልተኛ አትሌቶችና የኦሊምፒክ የስደተኞች ቡድን ይሳተፋሉ።
ኢትዮጵያም በዋናነት በተለያዩ ርቀቶች በሚደረጉ የአትሌቲክስ የስፖርት ውድድሮች በ39 ስፖርተኞች የምትካፈል ሲሆን አትሌቶቹ ከሚያዚያ 2016 ዓ.ም አንስቶ ከፍተኛ ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ፈረንሳይ የኦሊምፒክ ተሳታፊ ሀገራትን ቀይ ምንጣፍ በመዘርጋት እየተቀበለቻቸው ሲሆን ለታላቁ ድግስ 9 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንዳደረገች መረጃዎች ያመለክታሉ።
የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የመክፈቻ ስነ ስርዓት በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ30 አንስቶ የሚከናወን ሲሆን የመክፈቻ ስነ ስርዓቱ በኦሊምፒክ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከስታዲየም ውጪ በወንዝ ዝላይ ይደረጋል።
በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ 10 ሺህ 500 ስፖርተኞች በሰሜናዊ ፈረንሳይ በሚገኘው ሴይን ወንዝ ላይ በመርከብ የ3 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር ጉዞ በማድረግ የመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ይከናወናል።
አትሌቶች የመርከብ ጉዟቸው ከኦስተርሊትዝ ድልድይ ጀምረው በኖትሬ-ዳም ካቴድራል፣ ሉቭር ሙዚየም ፣ 'ፓላስ ዴላ ዲ ኮንኮርድ' እየተባለ በሚጠራው የሕዝብ አደባባይ፣ ጥንታዊ ሕንጻዎች ባሉበት 'ኢንቫሊዴስ' መንደርና ታሪካዊውን ኤይፍል ታወር አቋርጠው 'ትሮካዴሮ' የተሰኘው ስፍራ ላይ መዳረሻቸውን ያደርጋሉ።
"የብርሃን ከተማ" እየተባለች የምትጠራው ፓሪስ በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ በብርሃን የደመቀ ዝግጅት ታሳያለች ተብሎ ሲጠበቅ በስነ ስርዓቱ ላይ ሙዚቀኞችና 400 ዳንሰኞችን ጨምሮ 3 ሺህ ሰዎች ስራቸውን በቦታው ያቀርባሉ።
የማሊና የፈረንሳይ ጥምር ዜግነት ያላት የ29 ዓመቷ ድምጻዊና የዜማ ደራሲ አያ ናካሙራ በመክፈቻው ስነ ስርዓት ስራዋን ታቀርባለች።
አሜሪካዊቷ ሌዲ ጋጋና ካናዳዊቷ ኮከብ ሴሊን ዲዮን የሙዚቃ ስራቸውን ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የመክፈቻ ስነ ስርዓቱን 300 ሺህ ተመልካች እንደሚከታተለው የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።
እስከ አሁን ማንነቱ ያልታወቀ ግለሰብ የኦሊምፒክ ችቦውን ይለኩሰዋል ተብሎ እንዲሚጠበቅ የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ላይ ናቸው።
ከኦሊምፒክ መክፈቻ ስነ ስርዓቱ በፊት ባሉት ቀናት የወንዶችና የሴቶች የእግር ኳስ ውድድር፣ ራግቢ፣ የእጅ ኳስና የኢላማ ተኩስ ስፖርቶች ተጀምረዋል።
33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል።