ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት አቅጣጫ መሰረት ተጎጂዎችን የመደገፍና የማቋቋም ስራ በትኩረት እየተከናወነ ነው - አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት አቅጣጫ መሰረት ተጎጂዎችን የመደገፍና የማቋቋም ስራ በትኩረት እየተከናወነ ነው - አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሰጡት አቅጣጫ መሰረት በጎፋ ዞን በገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ከሰብዓዊ ድጋፍ ጀምሮ የመልሶ ማቋቋም ስራው በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት በጎፋ ዞን በገዜ ጎፋ ወረዳ ሀምሌ 15/2016 በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ የተጎዱ ወገኖችን የመደገፍ ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ይሄንን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት አቅጣጫ መሰረት የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ያሉበት ቡድን በአካባቢው ተገኝቶ ማህበረሰቡን የማፅናናት፣ የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎቶችና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን የመለየት ስራ አከናውነዋል፡፡
የህይወት አድን ስራው እየቀጠለ በሚገኝበት በዚህ ወቅትም የ226 ዜጎች ህይወት እንደጠፋ የተረጋገጠ ሲሆን ፍለጋውም መቀጠሉን ጠቁመዋል።
የተፈናቃይ ቁጥርን በሚመለከት በአደጋው ክስተት ዙሪያ እንዲነሱ የተደረጉትን 600 ሰዎችን ጨምሮ በቀጣይ መነሳት ያለባቸው ተጨማሪ 6 ሺህ የሚጠጉ ተጋላጮች የተለዩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) እንደገለጹት ከሰብዓዊ ድጋፍ ተግባራት ጎን ለጎን የመልሶ ማቋቋም ስራዎች በተደራጀና በባለሙያ ጥናት በሚለይ ቦታ ለማከናወን ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው።
እየተደረገ ያለው ሰብዓዊ ድጋፍም ከክልሉ መስተዳደር፣ ከዞኖችና ከማህበረሰብ በተጨማሪ ከፌዴራል መንግስት አካላት፣ ከሌሎች የክልል መስተዳደሮች፣ ተቋማትና ዜጎች ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን አጋር አካላትም በዩ.ኤን ኦቻ አስተባባሪነት ምግብና ምግብነክ ያልሆኑ ድጋፎች እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከአጭር ጊዜ አኳያ ለሚከናወኑ የህይወት አድንና መልሶ የማቋቋም ስራዎች ፈፃሚ አካላት የተለዩ ሲሆን የአሰቸኳይ ጊዜ አደጋ ምላሽ የማስተባበርና የማቀናጀት አደረጃጀትም ተፈጠሯል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አደጋው ከተከሰተበት እለት ጀምሮ ኢትዮጵያዊነትን አጉልቶ ያሳየ ሰብዓዊ ድጋፍ ሁሉንም አካላት አመስግኗል።
ችግሩንም በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው ርብርብ ድጋፋችሁ እንዳይለይ ከወዲሁ እንጠይቃለን ሲሉም ገልጸዋል፡፡