የአፍሪካ አገራት ከብሉ ኢኮኖሚ ትሩፋቶች ለመቋደስ ለውሃ ሀብቶች ጥበቃ በልዩ ትኩረት መስራት አለባቸው - የአፍሪካ ሕብረት - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ አገራት ከብሉ ኢኮኖሚ ትሩፋቶች ለመቋደስ ለውሃ ሀብቶች ጥበቃ በልዩ ትኩረት መስራት አለባቸው - የአፍሪካ ሕብረት
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦የአፍሪካ አገራት ከብሉ ኢኮኖሚ ትሩፋቶች ተቋዳሽ ለመሆን የውሃ ሀብቶች ጥበቃ ላይ በተለየ ትኩረት መስራት እንደሚጠበቅባቸው የአፍሪካ ሕብረት አሳሰበ።
አራተኛው የአፍሪካ የባህርና የውቅያኖስ ቀን ዛሬ በአፍሪካ ሕብረት ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ተከብሯል።
የአፍሪካ ሕብረት የዘላቂ ከባቢ አየርና ብሉ ኢኮኖሚ ዳይሬክተር ሃርሰን ንያምቤ ንያምቤ ብሉ ኢኮኖሚ (ውቅናኖስ፣ባህርና ሌሎች የውሃ ሀብቶች) ለአፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ እድገት ትልቅ አቅም የሚፈጥር ዘርፍ ነው ብለዋል።
የአፍሪካ ሕብረት የብሉ ኢኮኖሚና የማሪታይም ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ ወደ ትግበራ ማስገባቱን አንስተው ለአባል ሀገራትም ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል።
ለትራንስፖርት፣ ለንግድና ለአገልግሎት ዘርፍ እድገት እንዲሁም ለአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራ ውጤታማነት ወሳኝ አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክተዋል።
ይሁንና የአየር ንብረት ለውጥና በውሃ ብዝሃ ሕይወት ላይ የሚያጋጥም አሲዳማነት በብሉ ኢኮኖሚ ልማት ትልቅ ፈተናና ከጋረጡ ጉዳዮች መካከል እንደሚጠቀሱ ተናግረዋል።
በዘርፉ ያሉ ፈተናዎች መፍትሔ ለማበጀት የጋራ ጥረት እንደሚያስፈልግና ሀገራት ዘላቂነት ያለውን የውሃ ሀብት አጠቃቀም ለማሳካት ለብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።
የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) የአፍሪካ ቀጣናዊ አገልግሎት ማዕከል ተጠባባቂ ዳይሬክተር ኖኒ ማፋቡኔ በበኩላቸው የብሉ ኢኮኖሚ ዘርፍ ለአፍሪካ ብዙ እድሎች ይዞ ቢመጣም የተለያዩ ፈተናዎች እንዳሉበት ገልጸዋል።
ሕገ ወጥ ዓሳ ማስገርና ብክለት የውሃና ውሃ አዘል ሀብቶችን ሕልውና አደጋ ላይ እንዳይጥሉ የክብካቤና የጥበቃ ስራ ትኩረት እንደሚያሻውና ለዚህ የጋራ ትብብር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
ዩኤንዲፒ ለአፍሪካ ብሉ ኢኮኖሚ እድገት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የአፍሪካን የግሉ ዘርፍ ወክለው ንግግር ያደረጉት የዓሳና አሳ ውጤቶች አምራች የሆነው የካቲ ፋርምስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሎቪን ኮቡሲንግዬ አፍሪካ በብሉ ኢኮኖሚ ዘርፍ በጥሩ መንገድ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል።
የብሉ ኢኮኖሚ ዘርፍ አጀንዳ 2063ን ጨምሮ በአፍሪካ ደረጃ የተያዙ አጀንዳዎችን ከዳር ለማድረስና የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል።
የግሉ ዘርፍም አፍሪካ የውሃ ሀብቶችን በዘላቂነት ተጠቅማ በኢኮኖሚ ለማደግ የያዘችውን ውጥን እውን ለማድረግ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በአፍሪካ ሕብረት የኖርዌይ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ ሲን ኤሚሊ ብዮርንራ፤ ከዕለት ተዕለት ሕይወታችን ጋር የተሳሰሩት የውሃ ሀብቶች ረሃብን፣ ድርቅንና የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል እድገትና ልማትን ለማምጣት ወሳኝ ናቸው ብለዋል።
ኖርዌይ በብሉ ኢኮኖሚ ዘርፍ የአፍሪካ አጋር መሆኗን ጠቅሰው አህጉሪቷ በዘርፉ ለማሳካት የያዘቻቸውን ግቦች መደገፏን እንደምትቀጥል አመልክተዋል።
በአፍሪካ የባህርና ውቅናያኖስ ቀን አከባበር ላይ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን አመራሮች፣ የሕብረቱ አባል ሀገራት ተወካዮች፣ የዘርፉ ተዋንያንና የልማት አጋሮች ተገኝተዋል።
የአፍሪካ የባህርና ውቅያኖስ ቀን የአፍሪካ ውሃማ አካላት ሳምንት መርሐ ግብር አካል ነው።
ቀኑ በአፍሪካ ያሉ ውሃና ውሃ አዘል ሀብቶች ዘላቂ በሆነ መንገድ መጠቀም ከተቻለ ለኢኮኖሚ እድገት፣ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥና ለከባቢ አየር ጤናማነት ያለውን ጠቀሜታ ማስገንዘብን አላማ አድርጓል።
በተጨማሪም የብሉ ኢኮኖሚ ሀብቶችን ለመጠቀም የጋራ ትብብር ማሳደግ እንዲሁም ሴቶችና ወጣቶችንን ጨምሮ ሁሉን አሳታፊ ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባ አጽንኦት ተሰጥቶታል።
የአፍሪካ ባህርና ውቅያኖስ ቀን ከእ.አ.አ 2021 አንስቶ በመከበር ላይ ይገኛል።
"የአፍሪካ ብሉ ኢኮኖሚ ሕዳሴን ማረጋገጥ" በሚል መሪ ቃል ከሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም አንስቶ ሲከበር የቆየው የአፍሪካ ብሉ ኢኮኖሚ ሳምንትም ዛሬ ተጠናቋል።
ሳምንቱን በማስመልከት ላለፉት ቀናት ብሉ ኢኮኖሚን የተመለከተ አውደ ጥናት ተካሄዷል።
ብሉ ኢኮኖሚ የውቅያኖስ፣ የባህርና ሌሎች የውሃ ሀብቶችን ለኢኮኖሚ እድገት መጠቀም ላይ ትኩረቱን ያደረገ የኢኮኖሚ ዘርፍ ነው።