ቀጥታ፡

የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳደር በገዜ ጎፋ ወረዳ የመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ አደረገ

ጂንካ፤ሐምሌ 18/2016 (ኢዜአ)፡- የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳደር በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የተለያዩ ድጋፎችን አደረገ።

የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳደር በስሩ ያሉ ስድስት ወረዳዎችና አንድ ከተማ አስተዳደር በጋራ በመቀናጀት ነው ድጋፍ ያደረጉት።

መዋቅሮቹ "ለወገን ደራሽ ወገን ነው" በሚል መሪ ሃሳብ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የተለያዩ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።

በዚህን ጊዜ የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማልኮን ጨምሮ ሌሎች የስራ ኃላፊዎችና የዞኑ ተወካዮች  አደጋው በተከሰተበት ስፍራ በመገኘት ተጎጂ ወገኖችን አጽናንተዋል ። 

በአካባቢው በተከሰተው ድንገተኛ አደጋ በጠፋው የሰው ሕይወት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸው፣ በአደጋው ቤተሰቦቻቸውን በሞት ላጡ ወገኖቻችን መፅናናትን ተመኝተዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳደር እንዲሁም የከተማና የገጠር ወረዳ መዋቅሮች በመቀናጀት ከ1 ሚሊዮን 199 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የተለያዩ የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን አቶ ማዕከል ገልጸዋል።

ዞኑ በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የሚያደርገውን ሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።


 

የጎፋ ዞን አስተዳደርን በመወከል ድጋፉን የተረከቡት አቶ ታደለ ያዕቆብ "የደቡብ ኦሞ ዞን አመራር አባላት ረጅም ርቀት በመጓዝ ሀዘናችንን ስለተካፈላችሁ በተጎጂዎች ስም እናመሰግናለን" ብለዋል።

በአካባቢው የደረሰው ጉዳት አስከፊ መሆኑን ጠቁመው በአሁኑ ወቅት ተጎጂዎችን የማጽናናትና ሰብኣዊ ድጋፎችን የማድረግ ስራዎች በተቀናጀ መልኩ መቀጠላቸውንም ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም