የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞቹን ፍላጎት ለማሟላት የዲጂታል አገልግሎቶችን በተሻለ መልኩ እያቀረበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞቹን ፍላጎት ለማሟላት የዲጂታል አገልግሎቶችን በተሻለ መልኩ እያቀረበ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞቹን ፍላጎት ለማሟላት የዲጂታል አገልግሎቶችን በተሻለ መልኩ እያቀረበ መሆኑን የባንኩ የሰው ኃይል ምክትል ፕሬዚዳንት ኤፍሬም መኩሪያ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በርካታ አገልግሎቶችን መስጠት የሚያስችል ሲቢኢ ብር ፕላስ የተሰኘ መተግበሪያን በይፋ ስራ አስጀምሯል።
የባንኩ የሰው ኃይል ምክትል ፕሬዚዳንት ኤፍሬም መኩሪያ፤ ባንኩ የደንበኞቹን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ የተለያዩ የዲጂታል አማራጮችን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚሀም ደንበኞች ባሉበት ሆነው የባንኩን አገልግሎት በቀላሉ እንዲያገኙ እያስቻለ ነው ብለዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በባንኩ ከተደረጉ የገንዘብ ዝውውሮች 72 በመቶ የሚሆነው በዲጅታል አማራጮች የተከናውኑ መሆኑን ገልጸዋል።
የሲ ቢኢ ብር አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥርም አሁን ላይ 12 ሚሊየን መድረሱን ጠቅሰዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተርና የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ትዕግስት ሃሚድ፤ በዲጂታል አገልግሎት ቀዳሚ በመሆን ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 እንዲሳካ የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
የሲቢኢ ብር ፕላስ መተግበሪያም ለደንበኞች በቀላሉና በተቀላጠፈ መልኩ በርካታ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ከመደበኛ የባንክ ሒሳብ ጋር የተሳሰረ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል እንደሆነ እና በርካታ የክፍያ ገንዘብ ዝውውር ማድረግ የሚያስችል ነው ተብሏል።
የአየር ሰዓት ጥቅል ግዢ መፈጸም፣ ገንዘብ ወደ ቡድን መላክ፣ወደ ሌሎች ባንኮች ገንዘብ ማስተላለፍ እና የታቀደ ክፍያ መፈጸምን ጨምሮ ሌሎችንም አገልግሎቶች ያካተተ መሆኑ ታውቋል።