ቀጥታ፡

በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ በቅርበት እየተከናወነ ነው - ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር)

ሀዋሳ፤ ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ቤተሰቦቻቸውን ላጡና ለተፈናቀሉ ወገኖች አስቸኳይና ዘላቂ ድጋፍ ለማድረግ ሁሉም የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በቅርበት እየሰሩ መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ።

የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ ከአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽንና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ጋር በመሆን በደቡብ ኢትዮጵያ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ ቤተሰቦቻቸውን ላጡና ለተፈናቀሉ ወገኖች በሚደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍ ላይ ምክክር አድርገዋል።

በዚህም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ(ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ አደጋው ከተከሰተ በኋላ በመንግስት በኩል ጉዳቱን ለመቀልበስ የተደረገው ጥረት አመርቂ መሆኑም ተገምግሟል።

በአሁን ወቅት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጀምሮ በተሰጠው ትኩረት፣ የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽንና የጤና ሚኒስቴርን ጨምሮ ሁሉም የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በሥፍራው በመገኘት በቅርበት እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖችን አስከሬን የማውጣትና በሥርዓት እንዲቀበሩ የማድረጉ ተግባር አሁንም በርብርብ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ጉዳት የደረሰባቸውን ሕክምና የሚሹ ሕፃናትና ሌሎች ወገኖችን በመለየት አፋጣኝ ህክምና እየተሰጣቸው መሆኑን ገልፀው፤ የዕለት ደራሽ ምግብና መጠለያ ድጋፍም እንዲሁ በተደራጀ መልኩ እየቀረበ መሆኑን አውስተዋል።

አደጋው ከደረሰበት ዕለት ጀምሮ በተለይ የነፍስ አድንና ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎችን የማውጣት ሥራው በርብርብ የተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ በአካባቢውና በመልክዓ ምድሩ ሁኔታ በሰው ኃይል ብቻ ለመስራት ግድ ማለቱን ጠቅሰዋል።

ቦታው ማሽነሪዎችንና ተሽከርካሪዎችን ወደ ሥፍራው ለማስገባት አመቺ እንዳልሆነ ጠቁመው፤ በአካባቢው ማሽነሪዎችና ተሽከርካሪዎች በማንቀሳቀስ ጫና መፍጠር ዳግም የመሬት መንሸራተት አደጋ ሊያስከትል የሚችል መሆኑን ከባለሙያዎች በተሰጠ መረጃ መሰረት በሰው ሃይል ብቻ እንዲሰራ መደረጉን ተናግረዋል።

ለአደጋው ምላሽ ለመስጠት የመንግስት መዋቅሮችን ጨምሮ ሁሉም የኢትዮጵያዊ ማንነትን በውል በሚገልፅ መልኩ ርብርብ እያደረጉ መሆኑን አብራርተዋል።

በአደጋው የተጎዱ ወገኖችን በዘላቂነት የማቋቋሙ ሥራም ሆነ ተመሳሳይ አደጋ እንዳይከሰት የመከላከሉ ተግባር በትኩረት እንደሚሰራም አስረድተዋል።

አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ዶክተር ሺፈራው ተክለማርያም በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በአደጋው እስከ አሁን 226 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

በአሁኑ ወቅት በአደጋው ቤተሰቦቻቸውን ላጡና ለተፈናቀሉ ዜጎች አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች፣ የህክምናና ሌሎች ድጋፎች በበቂ ሁኔታ መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

አደጋውን በዘላቂነት ለመቀልበስ እንዲሁም ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን ከሥፍራው አንስቶ ወደ ሌላ አካባቢ ለማስፈር በቂ የዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም ገልፀዋል።

በምክክሩ ላይ ከሁሉም የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች እንዲሁም የሌሎች የፌዴራልና የክልል ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም