ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በበጎ ፈቃድ ለ20 ሺህ ዜጎች ነፃ የህክምና አገልግሎት ሊሰጥ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በበጎ ፈቃድ ለ20 ሺህ ዜጎች ነፃ የህክምና አገልግሎት ሊሰጥ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በክረምቱ የበጎ ፈቃድ ለ20 ሺህ ዜጎች ነፃ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታወቀ።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፤ በሆስፒታሉ በመገኘት ችግኝ በመትከል አሻራቸውን አኑረዋል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግርም የጤና ባለሙያዎች በአካባቢ ጥበቃም ይሁን በማህበራዊ ጤና በቅንነት ማገልገል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በመሆኑም የሆስፒታሉ ሰራተኞች በክርምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለጌርጌሴኖን የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል የስነ-አዕምሮ ሕክምና ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አድንቀዋል።
የበጎ ፈቃድ ስራ የዘወትር አገልግሎት ሆኖ በመቀጠል አቅመ ደካሞችን፣ ህፃናትንና እናቶችን የመደገፍ ስራም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
የበጎ ፈቃድ ተግባራትን በማገዝና በመደገፍ ረገድ ጤና ሚኒስቴር የሚያደርገውን ድጋፍና እገዛ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ፤ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና የጤና ሳይንስ ኮሌጁ በጤናው ዘርፍ የላቀ ሚናቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ሆስፒታሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት የሚያበረክተው አስተዋጽኦም የላቀ በመሆኑ ባለሙያዎች ተባብርው ሚናቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።
የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፕሮፌሰር አንዷለም ደነቀ፤ ከዛሬ ጀምሮ "እሺ ለበጎ ተግባር" በሚል መሪ ሃሳብ ለአንድ ወር የሚቆይ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለ20 ሺህ ዜጎች ነፃ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት መታቀዱን ጠቅሰው በጌርጌሴኖን የአእምሮ ሕክምና ማዕከል ዘላቂ የሆነ የስነ-አእምሮ የሕክምና አገልግሎት እንሰጣለን ብለዋል።
የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በመቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማህበር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በዘላቂነት ዓመቱን ሙሉ እየሰጠ መሆኑ ተጠቅሷል።