የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በርካታ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ሲቢኢ ብር ፕላስ የተሰኘ መተግበሪያ ይፋ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በርካታ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ሲቢኢ ብር ፕላስ የተሰኘ መተግበሪያ ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በርካታ አገልግሎቶችን መስጠት የሚያስችል ሲቢኢ ብር ፕላስ የተሰኘ መተግበሪያን በይፋ ስራ አስጀምሯል።
በማስጀመሪያ መርኃ ግብሩ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተርና የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ትዕግስት ሃሚድ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሰው ኃይል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ፣ ሌሎች የባንኩ አመራሮችና ሠራተኞች ተገኝተዋል።
የባንኩ የሰው ኃይል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ባንኩ የደንበኞቹን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ የተለያዩ የዲጂታል አማራጮችን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።
ይህም ደንበኞች ባሉበት ቦታ ሆነው የባንኩን አገልግሎት እንዲያገኙ አስችሏል ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፥
የሲ ቢኢ ብር ተጠቃሚዎች ቁጥር 12 ሚሊየን መድረሱን ተናግረዋል።
ዛሬ ይፋ የሆነው የሲቢኢ ብር ፕላስ መተግበሪያም ለደንበኞች በርካታ አገልግሎቶችን መስጠት የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው፥ ለአጠቃቀም ምቹ ነው ብለዋል።
ቀድሞ ከነበረው የሲቢኢ ብር መተግበሪያ አንጻር በርካታ አገልግሎቶችን በተሻለ መልኩ እንዲሰጥ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው ተብሏል።
ከመደበኛ የባንክ ሒሳብ ጋር የተሳሰረ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል እንደሆነ እና በርካታ የክፍያ ገንዘብ ዝውውር ማድረግ የሚያስችል እንደሆነም ተገልጿል።