የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በሐረር የፌዴራል ፖሊስ ሆስፒታል የማስፋፊያ ፕሮጀክት ግንባታን ተመለከቱ - ኢዜአ አማርኛ
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በሐረር የፌዴራል ፖሊስ ሆስፒታል የማስፋፊያ ፕሮጀክት ግንባታን ተመለከቱ
ሐረር፤ ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በሐረር ፌዴራል ፖሊስ ሆስፒታል የማስፋፊያ ፕሮጀክት ግንባታን ተመለከቱ።
በመርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፋንታ፣ የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ረምዚ ሱልጣን፣ የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዓለሙ መግራ እና ሌሎች ከፍተኛ የአመራር አባላት ተሳትፈዋል።
በምስራቅ ኢትዮጵያ ለሚገኙ የሰራዊት አባላት እና ቤተሰቦች እየተሰጠ የሚገኘውን የህክምና አገልግሎት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚያስችለውን የሪፈራል ሆስፒታል የማስፋፊያ ግንባታ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ተመልክቷል።
የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ግንባታ የሚያከናውነው በመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ መሆኑን በኢንተርፕራይዙ የቢሮ ምህንድስና ቡድን መሪ ኢንጅነር ሄኖክ መላኩ ገልጸዋል።
ግንባታውን በታያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በጀት የሚገነባው የሆስፒታሉ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ባለ 8 ወለል ህንጻን ጨምሮ የጤና ባለሙያዎች መኖሪያ ቤትና ሌሎችንም መገልገያዎች የሚያካትት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ "በ3 ሺህ 200 ካሬ ሜትር ላይ እየተገነባ የሚገኘው ማስፋፊያው 65 በመቶ መድረሱን ጠቁመው፤ በአንድ ዓመት ውስጥ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት በትኩረትና በጥራት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
የሐረር ፌዴራል ፖሊስ ሆስፒታል በ1958 ዓ.ም እንደተመሰረተ ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያሳያል።