የአረንጓዴ አሻራና የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በትውልድ ቅብብሎሽ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የማህበራት ሚና ከፍተኛ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራና የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በትውልድ ቅብብሎሽ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የማህበራት ሚና ከፍተኛ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦የአረንጓዴ አሻራና የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በትውልድ ቅብብሎሽ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የማህበራት ሚና ከፍተኛ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ ገለጹ፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆን የአረንጓዴ አሻራና የክረምት በጎ ፍቃድ ማስጀመሪያ መርኃ ግብር አካሂዷል፡፡
በመርኃ ግብሩ የሚኒስቴሩ ተጠሪ ተቋማት፣ የተለያዩ የስፖርት፣ የኪነ ጥበብና የስነ ጥበብ ማህበራት ተሳትፈዋል፡፡
በዚሁ ወቅት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ እንደተናገሩት ሚኒስቴሩ የሀገር ፍቅር በሚገለጽባቸው የበጎ ፍቃድ አገልግሎትና የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ላይ በስፋት በመሳተፍ ላይ ይገኛል፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እነዚህ ተግባራት በትውልድ ቅብብሎሽ እንዲቀጥሉ ከስፖርት ፣ከኪነ ጥበብ፣ ሥነ ጥበብና ሌሎች ማህበራት ጋር በስፋት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህን ተከትሎ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአረንጓዴ አሻራና የክረምት በጎ ፍቃድ ማስጀመሪያ መርኃ ግብር ማካሄዱን ገልጸዋል፡፡
በመርኃ ግብሩ የችግኝ ተከላ፣ አነስተኛ ገቢ ላላቸው የተቋሙ ሰራተኛ ልጆች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍና የደም ልገሳ ተከናውኗል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በ2017 በጀት አመት ዘርፈ ብዙ የአረንጓዴ አሻራና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡
በስፖርትና በኪነ-ጥበብ ዘርፍ የተሰማሩ ማህበራት የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብርና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በትውልድ ቅብብሎሽ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ በጋራ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ይህን ተከትሎ በቅርቡ በአማራ ክልል ማህበራቱን በማሳተፍ የችግኝ ተከላና የአቅመ ደካሞችን መኖሪያ ቤቶች የማደስና ተግባር ይከናወናል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስፖርት ደጋፊዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ምንያህል ጌታቸው በበኩሉ ፤ ማህበሩ በአረንጓዴ አሻራ ልማት ከመሳተፍ ጎን ለጎን በስፖርቱ ድጋፍ ለሚፈልጉ ዜጎች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራ እያከናወነ መሆኑን ተናግሯል፡፡
በተለይም የሀገራቸውን ሠንደቅ አላማ ከፍ ያደረጉ ባለውለታዎች ችግር ባጋጠማቸው ወቅት ፈጥኖ በመድረስ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጉን በአብነት አንስቷል፡፡
እንደዚሁም አቅም ለሌላቸው ጀማሪ ስፖርተኞች የትጥቅና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ መሆናቸውን ጨምሮ ገልጿል፡፡
ማህበሩ በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የአምስት አቅመ ደካማ ዜጎችን መኖሪያ ቤት የማደስ፣ የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍና በአዲስ አመት ለ 1 ሺህ 500 ዜጎች ማዕድ ለማጋራት መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡
የተቋሙ ሰራተኛና የመርኃ ግብሩ አስተባባሪ የሆነው አቶ ተዋበ መኮንን ከዚህ ቀደም በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራና የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ላይ በንቃት መሳተፋቸውን በማስታወስ ዘንድሮም የጀመሩትን ስራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጧል፡፡