ቀጥታ፡

የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና አረንጓዴ ሽግግር ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት ገለጸ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦ የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና አረንጓዴ ሽግግር እንዲሁም በአለም አቀፍ ጌትዌይ ስትራቴጂ ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት ገልጿል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍፁም አሰፋ በ4ኛው ዓለም አቀፍ ፋይናንስ ለልማት ጉባኤ (FfD) የዝግጅት ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ከተገኙት የአውሮፓ ህብረት የአለም አቀፍ አጋርነት (INTPA) የዘላቂ ፋይናንስ ዳይሬክተር አንቲ ካርሁነን ጋር ተወያይተዋል።


 

በቅርቡ በጎፋ ዞን የደረሰው የመሬት ናዳ ባስከተለው አሰቃቂ የሰው ህይወት መጥፋት በአውሮፓ ህብረት ስም የተሰማቸውን ሀዘን ዳይሬክተሩ መግለጻቸውን ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንና አሁን ላይ ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ ፌደራል የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ጋር እየሰራ በሚገኘው ቡድን በኩል እየተሰራ እንደሆነ ገልፀዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍፁም አሰፋ በበኩላቸው ለአውሮፓ ህብረት ፈጣን ምላሽ አድናቆታቸውን ገልፀው ከአፋጣኝ ሰብአዊ ድጋፍ ጎን ለጎን ዘላቂ የአየር ንብረት መላመድ ስትራቴጂ እንደሚያስፈልግ አፅንዖት ሰጥተዋል።

በሁለትዮሽ ውይይቱ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር የምታደርገውን ጥረትም ተመልክቷል።

የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት በወሰዳቸው እርምጃዎች ላይ ማብራራታቸውም ተጠቁሟል።

በመሆኑም የሽግግር የፍትህ ስርዓት የህግ ማዕቀፍ ዝግጅት ሊጠናቀቅ መቃረቡን ገልጸው በተጨማሪም የብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋሙ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ወሳኝ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያን የሀገር ውስጥ ኢኮኖሚ ማሻሻያ I ላይ ገለፃ በማድረግ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ተወዳዳሪነት እና የኢንቨስትመንት መስህብነት በማጎልበት የተመዘገቡ ስኬቶችን አውስተዋል።

ኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የሀገር ውስጥ ግጭቶች እና በምስራቅ እና ደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ የተከሰቱ እንደ ድርቅ ያሉ የአየር ንብረት ነክ ጉዳዮች አንዳንድ የማሻሻያ ጥረቶች እንዲስተጓጎሉ እንዳረጉ አመላክተዋል፡፡

የሃገር ውስጥ የኢኮኖሚ ማሻሻያ II ሌላኛው የውይይቱ ትኩረት እንደነበርም በመረጃው ተጠቅሷል።

የአውሮፓ ህብረት የአለም አቀፍ አጋርነት (INTPA) የዘላቂ ፋይናንስ ዳይሬክተር አንቲ ካርሁነን የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና አረንጓዴ ሽግግር እንዲሁም በአለም አቀፍ ጌትዌይ ስትራቴጂን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን መግለጻቸውም ተመላክቷል።

በአውሮፓ ህብረት ሁለገብ አመታዊ አመላካች ፕሮግራም (MIP) ስር ለኢትዮጵያ የተመደበውን 650 ሚሊዮን ዩሮ አንዱ የድጋፉ አካል መሆኑን ማንሳታቸውም እንዲሁ።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍፁም አሰፋ የኢትዮጵያን በሁለገብ አመታዊ አመላካች ፕሮግራም (MIP) በማቀድና ትግበራ ላይ ማሳተፍ በሀገሪቱ ቅድሚያ በሚሰጣቸው የልማት እንቅስቃሴዎች ጋር እንዲጣጣም በማድረግ ረገድ ያለውን ጠቀሜታ አስገንዝበዋል።

ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ወሳኝ የሆነው የአውሮፓ ህብረት የበጀት ድጋፍ እንደገና እንዲጀመርም ጥሪ አቅርበዋል።

በአዲሱ የአውሮፓ ህብረት የደን ጭፍጨፋ-ነጻ ደንብ (EUDR) ስጋት እንዳደረባቸው መግለጻቸውም ተጠቅሷል።

የተጣደፈ ትግበራ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ቡና አምራቾችን ሊጎዳ እንደሚችል እና የአውሮፓ ህብረት የደን ጭፍጨፋ-ነጻ ደንብ (EUDR) ከአለም አቀፍ የአየር ንብረት ስምምነቶች ትክክለኛ የሽግግር መርሆዎች ጋር ሙሉ በሙሉ መጣጣም እንዳለበትም አንስተዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ የEUDR መስፈርቶችን ለማሟላት ያላትን ቁርጠኝነት ገልፀው ለትግበራው የሚረዳ ተጨማሪ ግዜ እንደሚያስፈልግ ማመላከታቸውን በመረጃው ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም