በከተሞቹ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ለገጽታ ግንባታና እድገት አስተዋጽኦ  እያደረጉ ነው  

ዲላ ፤ ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአርባምንጭ፣ ወላይታ ሶዶና ዲላ ከተሞች ህብረተሰቡን በማሳተፍ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች ገጽታን በመለወጥና እድገትን በማፋጠን አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን የየከተሞቹ  ከንቲባዎች አስታወቁ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ የ2016 በጀት አመት ዕቅድ አፈፃፀምና የ2017 ዕቅድ ዝግጅት ግምገማውን  በዲላ ከተማ አካሂዷል።

የአርባ ምንጭ፣ ወላይታ ሶዶና ዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች ግምገማውን ተከትሎ ለኢዜአ እንደገለጹት በከተሞቹ ህብረተሰቡን በማሳተፍ እየተከናወኑ ያሉ የመሰረተ ልማት ስራዎች ገፅታዎችን ትርጉም ባለው መልኩ እየቀየሩ ነው።

የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ገዛኸኝ ጋሞ እንደተናገሩት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከተማዋን ለነዋሪዎች ምቹና ጽዱ ለማድረግ በርካታ የልማት ተግባራት ተከናውነዋል።

በከተማው ከ390 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የ4 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ግንባታ፣ የጌጤኛ ድንጋይ ንጣፍ መንገድ ፣ ማፋሰሻ ቦዮችና መሸጋገሪያ ድልድዮች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ዘጠኝ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮርደር ልማት ስራ እየተፋጠነ መሆኑን ተናግረዋል።

የልማት ስራዎቹ የከተማውን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ እድገቱን ለማፋጠን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

በከተማው እየተከናወኑ ባሉ የልማት ስራዎች ላይ የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማጠናከር የከተማዋን ተወዳዳሪነትና ደረጃ ለማሳደግ የበለጠ እንደሚሰራ አመላክተዋል።

በተመሳሳይ በዲላ ከተማ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ለረጅም ጊዜ የህብረተሰብ ጥያቄ ምላሽ የሰጡ መሆናቸውን ያነሱት ደግሞ የከተማው አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዳንኤል ሽፈራው ናቸው።


 

በተለይም  በህብረተሰብ ተሳትፎ 36 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የውስጥ ለውስጥ መንገድ በማድረግ 22 ኪሎ ሜትሩን ጠጠር የማልበስ ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

ከአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ተሞክሮ በመውሰድ በከተማው ያረጁ አካባቢዎችን መልሶ ማልማት ላይ ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል።

እንዲሁም የእግረኛ መንገድ ግንባታ፣ በአረንጓዴ ልማት የማስዋብና ፕላን የማስጠበቅ ተግባራት እየተተገበሩ መሆናቸውን ጠቅሰው ስራው የከተማውን ገጽታ በመለወጥ  እያሳደገው ነው ብለዋል።

የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ጃጋና አይዛ በበኩላቸው ህብረተሰቡን በማሳተፍ በተከናወኑ የልማት ስራዎች የከተማውን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ የኢንቨስትመንት ፍሰትና ፍላጎት መጨመሩን ተናግረዋል።


 

በተለይ የከተማው ማህበረሰብ ውበትና ጽዳትን ባህሉ እንዲያድግ በተደረገ ጥረት አበረታች ውጤት መምጣቱን ጠቅሰው ይህም በመሰረተ ልማትና በቀልጣፋ አገልገሎት እንዲጠናከር መደረጉን ገልጸዋል።

የኮሪደር ልማት ከተሞችን ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ መሆኑን ያነሱት ከንቲባው የአዲስ አበባን ተሞክሮ በመውሰድ በመከናወን ላይ ያለው የኮልደር ልማት ስራ የከተማውን ገፅታ እየቀየረው ነው ብለዋል።

በቀጣይ የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማጠናከር ከተማዋን ተወዳዳሪና ተመራጭ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት እንደሚጠናከር አመላክተዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በበኩላቸው በተጠናቀቀው የበጀት አመት የከተሞችን ገጽታ ለመቀየርና ምቹ ለማድረግ ህብረተሰቡን በማሳተፍ መሰራቱን ተናግረዋል።


 

በዚህም በልማቱ ባለቤትነትን ከመፍጠር ባለፈ አዳዲስ አስተሳሰቦችን ለማስረፅ የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።

ከተሞች ተመራጭና ለኑሮ ምቹ እንዲሆኑ ለማስቻል እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጣቸውም የተሻለ እንዲሆን በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል።

በከተሞቹ እየተከናወኑ ካሉ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች በተጨማሪ የአዲስ አበባን የኮሪደር ልማት ተሞክሮ ተግባራዊ የመድረግ ስራ በተቀናጀ መንገድ መጀመሩን አመልክተዋል።

በክልሉ ከተሞችን እንደ ደረጃቸው በሚመጥናቸው መልኩ ለማልማት በጥናት ላይ የተመሰረተ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም