በዞኑ የመስኖ ልማትን ለማዘመን የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎች ለአርሶ አደሩ እየቀረቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የመስኖ ልማትን ለማዘመን የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎች ለአርሶ አደሩ እየቀረቡ ነው
መተማ ፤ ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦ በምዕራብ ጎንደር ዞን የመስኖ ልማት እንቅስቃሴን ለማዘመን የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች ለአርሶ አደሩ እየቀረቡ መሆናቸውን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የመስኖ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ቡድን መሪ አቶ አዲስዓለም ቢተው እንደተናገሩት፤ ዞኑ በአካባቢው ሰፊ በመስኖ መልማት የሚችልና ዓመቱን ሁሉ የሚፈሱ ወንዞች ያሉት ነው።
ለመስኖ ልማት ያለውን እምቅ ሀብት ለመጠቀምም አርሶ አደሩ የተለያዩ አማራጭ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቃሚ እንዲሆን የማቅረብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።
ቀደም ሲል በነዳጅ የሚሰሩ ጀኔሬተሮችን በማሰራጨት ማገዝ የተቻለ ቢሆንም የነዳጅ አቅርቦት እጥረት በመኖሩ ለአርሶ አደሩ ፈታኝ ሁኔታን ፈጥሮበት እንደነበር አስታውሰዋል።
በዚህም ችግሩን መፍታት የሚያስችል በፀሐይ ብርሃን መስራት የሚችል የውሃ መሳቢያ ሞተር ለአልሚ አርሶ አደሮች በድጋፍና በብድር መሰራጨቱን ገልፀዋል።
ለገንዳ ውሃ ከተማ፣ ለመተማና ለምዕራብ አርማጭሆ ወረዳዎች ከ6 ነጥብ5 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ስምንት የውሃ መሳቢያ ሞተሮች ለአልሚ አርሶ አደሮች ማቅረብ ተችሏል።
በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ አማራጭ ቴክኖሎጂዎችን የመትከልና የመገጣጠም ስራን በዘርፉ ባለሙያዎች መከናወኑን ገልፀው፤ በቀጣይ ቴክኖሎጂውን በሁሉም ወረዳዎች ለማዳረስ በቅንጅት እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪ አርሶ አደር ቢትወደድ ብርሃኑ ባለፉት ሰባት ዓመታት በመስኖ ልማት እየተሳተፉ ቢሆንም በነዳጅ ወጪ ምክንያት የሚጠብቁትን ያህል ተጠቃሚ እንዳልሆኑ አስታውሰዋል።
አሁን የተሰጣቸው በፀሐይ ብርሃን የሚሰራ የውሃ መሳቢያ ሞተር የነበረባቸውን ችግር የሚቀርፍ መሆኑን ተናግረዋል።
የውሃ መሳቢያ ሞተር ድጋፉ ለልማት ስራዬ ትልቅ መነሳሳት የሚፈጥርልኝ ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛው አልሚ አቶ አሊ ኢብራሂም ናቸው።
ዓመቱን ሙሉ የሚፈስ ወንዝና ለእርሻ ስራ የተመቸ መሬት ያላቸው በመሆኑ የሞተር ድጋፉ በስራቸው ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል።
ለነዳጅ ያወጡት የነበረው ወጪ ከፍተኛ እንደነበር የገለፁት አልሚው ቴክኖሎጂው በአጭር ጊዜ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ አቅም ለመፍጠር እንደሚያግዛቸውም ተናግረዋል።
በዞኑ በመስኖ መልማት የሚችል ከ240 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እንዳለም ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።