በክልሉ የመኖሪያ ቤት አከራይ ተከራይ አዋጅን ተግባራዊ ለማድረግ ወደ እንቅስቃሴ ተገብቷል- ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የመኖሪያ ቤት አከራይ ተከራይ አዋጅን ተግባራዊ ለማድረግ ወደ እንቅስቃሴ ተገብቷል- ቢሮው
ቦንጋ ፤ ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመኖሪያ ቤት አከራይ ተከራይ አዋጅን ለማስተግበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናቀው ወደ እንቅስቃሴ መገባቱን የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ አስታወቀ።
ተከራዮችና አከራዮች በበኩላቸው አዋጁ የአከራይና ተከራይን መብትና ጥቅም የሚያስከብር በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባም ተናግረዋል።
በቢሮው የቤቶች ሕንፃ ልማትና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ ከበደ እንደገለጹት፤ አዲሱን የመኖሪያ ቤት አከራይ ተከራይ አዋጅን በክልሉ ለማስተግበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናቀው ወደ ተግባር ተገብቷል።
በዚህም ለህብረተሰቡ ግንዛቤን የማስጨበጥ፣ ለምዝገባ የሚያገለግሉ የተለያዩ ቅጾችን እና የአከራይ ተከራይ የባህር መዝገብን የማዘጋጀት ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
የአዋጁ አተገባበር በዞን ከተሞች ተጀምሮ በሂደት እንደሚሰፋ ገልጸው፣ በተያዘው ሐምሌ ወር በስድስት የዞን ከተሞች ምዝገባውን ለማጠናቀቅ መታቀዱን ጠቁመዋል።
አዋጁ የአከራይና ተከራይን መብትና ግዴታዎች በዝርዝር ያስቀመጠ በመሆኑ የሁለቱንም ጥቅምና መብት ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ያስጠብቃል ነው ያሉት።
ከዚህ ቀደም አዋጁ ባለመኖሩ አከራዩ በፈለገበት ጊዜ ዋጋ የሚጨምርበትና ተከራዩን በማስወጣት በተከራይ ላይ ጫና የሚፈጥርበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰዋል።
አዋጁ ይህን በማስቀረት አከራይና ተከራይ ውል እንዲገቡና ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።
በአዋጁ መሰረት የኪራይ ክፍያ በባንክና ዲጂታል በሆነ መንገድ የሚፈጸም መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ለዚህም ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
አዋጁን አስመልክተው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የቦንጋ ከተማ ነዋሪ አቶ ኬሮ በላቸው እና ወጣት አሰግድ ኃይሌ አዋጁ አከራይና ተከራይን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ለበርካታ ዓመታት በኪራይ ቤት እየኖሩ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ኬሮ፣ አስከዛሬ አስገዳጅ ውል ባለመኖሩ ተከራይ በፈለገበት ጊዜ ዋጋ የሚጨምርበትና ከቤቱ የሚያስለቅቅበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰዋል።
አዋጁ በዚህ ምክንያት ሊፈጠር የሚችለውን አለመግባባት እና በተከራይ ላይ የሚያደርሰውን ጫና በመቀነስ በኩል የጎላ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
ወጣት አሰግድ ሀይሌ በበኩሉ አዋጁ በአከራይና ተከራይ መካከል ህግና ስርዓትን መሰረት ያደረገ ግንኙነት ስለሚፈጥር ሁለቱንም ተጠቃሚ ያደርጋል ብሏል።
አቶ ክንፈ ገብሬ የተባሉ ቤት አከራይ በበኩላቸው አዋጁ የአከራይና ተከራይን መብት ከግምት ያስገባ በመሆኑ በማህበራዊ ግንኙነታቸው ተከባብረው እንዲኖሩ ያደርጋል ብለዋል።
አከራይ የተከራይን ማንነት እንዲያውቅና ተከራዩም "የኪራይ ዋጋ ይጨመርብኛል" ከሚል ስጋት እንዲወጣ ስለሚያደርግ ለተግባራዊነቱ ሁሉም አስተዋፅኦ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም አዲሱን የመኖሪያ ቤት አከራይ ተከራይ አዋጅ ማጽደቁ ይታወሳል።