ቀጥታ፡

በቋራና መተማ ወረዳዎች የተገነቡ ተንጠልጣይ የመሸጋገሪያ ድልድዮች ችግራቸውን እንደፈታላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ 

መተማ ፤ ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦ በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራና መተማ ወረዳዎች የተገነቡ ሁለት ተንጠልጣይ የመሸጋገሪያ ድልድዮች በክረምት ወቅት በወንዝ ሙላት ይደርስባቸው የነበረውን  ችግር  እንደፈታላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ።

በሁለቱ ወረዳዎች ከ10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ተንጠልጣይ የመሸጋገሪያ ድልድዮች ተገንብተው  ለህዝብ አገልግሎት ክፍት መሆናቸውን የዞኑ መንገድ መምሪያ አስታውቋል።

በቋራ ወረዳ የአብተጋሆ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ትዛዙ አየነው ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ የሻሆ ወንዝ በክረምት ወቅት እየሞላ  በቀበሌው ህዝብ ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድር እንደነበር አስታውሰዋል።

በዚህም ወንዙን ለማቋራጥ በሚደረግ ሙከራ በተደጋጋሚ የሰው ህይወት መጥፋትና ንብረትም እየተወሰደባቸው ይቸገሩ  እንደነበር ጠቅሰዋል።

ዘንድሮ የድልድዩ መገንባት ከዚህ ችግር ከማለቀቁም በላይ ለከፍተኛ  ህክምና የሚላኩ ወላድ እናቶችንና ታካሚዎችን ለማድረስ ብሎም ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።

የገንዳ ውሃ ወንዝ ለበርካታ ዜጎች ህይወት መጥፋት ምክንያት ነበር  ያሉት ደግሞ  በመተማ ወረዳ የመቃ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሰጠኝ ወርቁ ናቸው።

መሸጋገሪያ ድልድይ ባለመኖሩ በተለይ ወንዙ ከሐምሌ ወር ጀምሮ ሲሞላ ለአደጋ ሲያጋልጥ እንደቆየ  አስታውሰው፤ አሁን ላይ የድልድዩ መገንባት የሰዎችን ህይወት መታደግ ያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል።

ድልድዩ ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃቱ ለቀበሌው ህዝብ እፎይታ ከመስጠቱም በላይ ከሌሎች ቀበሌ ነዋሪዎች ጋር የሚኖራቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነትን የሚያጠናክር መሆኑን አንስተዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን መንገድ መምሪያ ኃላፊ አቶ አባይነህ ወረታ፤ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በ10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ በጀት ሁለት ተንጠልጣይ ድልድዮች ተገንብተው  ለህዝብ አገልግሎት ክፍት መሆናቸውን አስታውቀዋል።


 

በዚህም በ5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በጀት  በቋራ ወረዳ ሻሆ ወንዝ ላይ የተገነባው  ተንጠልጣይ ድልድይ  1 ነጥብ 6 ሜትር ስፋትና 100 ሜትር ርዝመት ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በመተማ ወረዳ መቃ ቀበሌ በገንዳ ውሃ ወንዝ ላይ በ5 ሚሊዮን ብር በጀት የተገነባው ደግሞ  88 ሜትር ርዝመት እንዳለው ተናግረዋል።

በሁለቱም ወረዳዎች የተገነቡት ተንጠልጣይ ድልድዮች በዘጠኝ ቀበሌዎች የሚገኙ ነዋሪዎችን ክረምት ከበጋ ለማገናኘት የሚያስችሉ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የነበረውን ችግር በመቋቋም ተንጠልጣይ የመሸጋገሪያ ድልድዮቹን ግንባታ በማጠናቀቅ ለህዝብ አገልግሎት ለማብቃት የተደረገው ርብርብ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ድልድዮቹ ለአካባቢው ማህበረሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት መፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸውም ብለዋል። 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም