ኢትዮጵያ በብሪክስ ወጣቶች ጉባኤ ላይ እየተሳተፈች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በብሪክስ ወጣቶች ጉባኤ ላይ እየተሳተፈች ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በብሪክስ ወጣቶች ጉባኤ ላይ እየተሳተፈች ነው።
በራሽያ የኡሊያኖስክ ግዛት እየተካሄደ በሚገኘው 10ኛው የብሪክስ ወጣቶች ጉባኤ ላይ በኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፉአድ ገና የተመራ የልዑክ ቡድን እየተሳተፈ ይገኛል።
ጉባኤው በብሪክስ ማዕቀፍ ስር የአባል አገራቱን የወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ አላማ ያደረገ መሆኑም ተገልጿል።
10ኛው የብሪክስ ወጣቶች ጉባኤ በትምህርትና ስልጠና፣ ሳይንስ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ በጤና፣ በስፖርትና በኪነጥበብ ዙሪያ እየመከረ እንደሚገኝም ተመላክቷል።
ጉባኤው በብሪክስ አባል አገራት መካከል በወጣቶች ዘርፍ ያለውን ትብብርና አጋርነት ለማጠናከር በር የሚከፍት እንደሆነም የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት መረጃ ያሳያል።
በጉባኤው ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሁሉም የብሪክስ አባል አገራት የተወከሉ የወጣት አመራሮችና ሚኒስትሮች እየተሳተፉ እንደሚገኝም ተጠቅሷል።
ኢትዮጵያ በጉባኤው ስትሳተፍ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፉአድ ገና በብሪክስ የወጣቶች ምክርቤት ስብሰባ ላይ የተሳተፉ ሲሆን በብሪክስ የሚኒስትሮች ጉባኤ ላይም የሚሳተፉ እንደሆነም ተገልጿል።
ፕሬዝዳንቱ ከጉባኤው ጎን ለጎን የኢትዮጵያን ወጣቶች ተጠቃሚ በሚያደርጉ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን የትብብር ማዕቀፎች ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ጉባኤው ከሀምሌ 15 ቀን 2016 ጀምሮ በመካሄድ ላይ መሆኑንና እስከ ሀምሌ 19 ቀን 2016 ድረስ እንደሚቀጥልም በመረጃው ተመላክቷል።