ቀጥታ፡

የበዓሉ ታዳሚዎች በቆይታቸው ፍፁም ሰላማዊና የተሳካ ጊዜ እንዲያሳልፉ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጓል -- ከንቲባ ከድር ጁሃር

ድሬዳዋ ሐምሌ 17/2016--የዓመታዊው የቁሉቢ ገብርኤል በዓል ታዳሚዎች በድሬዳዋ ሰላማዊና የተሳካ ቆይታ እንዲኖራቸው አስተዳደሩ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን ከንቲባ ከድር ጁሃር አስታወቁ።

የፊታችን ሀምሌ 19 ቀን 2016 የሚከበረው የቁሉቢ ገብርኤል በዓል ላይ በርካታ ሰዎች የሚሳተፉ ሲሆን፤ የበዓሉ ታዳሚዎች ከሚያርፉባቸው ከተሞች አንዷ ድሬዳዋ ናት። 

ከንቲባ ከድር ጁሃርን ጨምሮ የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራር አባላት ለዓመታዊው የቁሉቢ ገብርኤል ንግስ በዐል ወደ ድሬዳዋ እየገቡ ለሚገኙ ታዳሚዎች አቀባበል አድርገዋል።

በዚሁ መሰረት በበዓሉ ላይ ለመታደም የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ተወካይና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ ናትናኤልና ሌሎች አባቶች ድሬዳዋ ሲገቡ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

የኃይማኖት አባቶቹም ድሬዳዋ ከገቡ በኋላ የከተማው አሸዋ ገበያ የደረሰውን አደጋ የተመለከቱ ሲሆን፤ ቤተክርስቲያኗ ተጎጂዎችን መልሶ በማቋቋም ተግባር ላይ የድርሻዋን እንደምትወጣ ተናግረዋል።

ከኃይማኖት አባቶቹ ባለፈ በዓሉ ላይ ለመታደም ድሬዳዋ እየገቡ የሚገኙ ሰዎች በከተማው መግቢያ ላይ ተገኝተው ተቀብለዋል።

በዚሁ ጊዜ ከንቲባ ከድር ጁሃር እንደተናገሩት፤ የፍቅር፣ የአንድነት እና የሰላም ከተማ የሆነችው ድሬዳዋ እንግዶቿ በቆይታቸው ስኬታማ ጊዜ እንዲያሳልፉ በትጋት እየሰራች ነው ብለዋል።


 

የበዓሉ ታዳሚዎች ያለምንም ችግር በዓሉን እንዲያከብሩ እና ድሬዳዋ ያሏትን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህቦች እንዲጎበኙ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጓን ገልፀዋል።

"በዐሉ ያማረና የተሳካ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እናደርጋለን" ብለዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ፓሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር አለሙ መግራ፣ የድሬዳዋ ፓሊስ ከምስራቅ ኢትዮጵያ የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለበዓሉ ድሬዳዋ የገቡ እንግዶች በቆይታቸው ሰላማዊ እና ስኬታማ ጊዜ እንዲያሳልፉ ፓሊስ እና የምሽት ታክሲ አሽከርካሪዎች አስፈላጊውን መረጃ በመስጠት እና በመተባበር ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ ብለዋል።

የበዓሉ አክባሪዎች ከትናንት ጀምሮ በብዛት ድሬዳዋ በመግባት ላይ ናቸው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም