ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የተጨዋቾች ዝውውርና የክለቦች የክፍያ አስተዳደር መመሪያ በማያከብሩ የሊጉ ክለቦች ላይ እርምጃ ሊወስድ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የተጨዋቾች ዝውውርና የክለቦች የክፍያ አስተዳደር መመሪያን በሚጥሱ የሊጉ ክለቦች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አሳሰበ።

የ2017 ዓ.ም.የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም መጀመሩ ይታወቃል። 

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበርና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተጨዋቾች ዝውውርና የክለቦች የክፍያ አስተዳደር መመሪያ አፈጻጸምን አስመልክቶ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ችግሮችን የተመለከተ ጥናት ከሁለት ዓመት በፊት ማስጠናቱ የሚታወስ ነው።

ከጥናቱ የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል አንዱ ክለቦች ያላቸው የፋይናንስ አስተዳደር እንዲሻሻል ምን መደረግ አለበት? የሚለው ላይ ሲሆን ጥናቱን መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የክፍያ ሥርዓት አስተዳደር መመሪያ ተዘጋጅቷል።

ይህ መመሪያ በሚያዝያ ወር 2016 ዓ.ም ማኅበሩ ባካሄደው 4ኛው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ጸድቋል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ፤  መመሪያው ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ከተጀመረው የ2017 ዓ.ም.የተጨዋቾች የዝውውር መስኮት ጀምሮ ተፈጻሚ መሆኑን ገልፀዋል።

በመመሪያው አማካኝነት ክለቦች የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዝውውር ውል ሳያጸድቅ ለተጨዋቾች አስቀድመው የቅድመ ክፍያ መፈጸምና በቼክ ገንዘብ መክፈል እንደማይችሉ አመልክተዋል።

በተጨማሪም ክለቦች በዓመት ለተጨዋቾችና የአሰልጣኞች ቡድን አባላት ደመወዝና ጥቅማጥቅም ከ57 ሚሊየን 750 ሺህ ብር በላይ ክፍያ መፈጸም አይችሉም ብለዋል።

የሊጉ ክለቦች የተቀመጡትን አሠራሮች የሚጥሱ ከሆነ ከገንዘብ ቅጣት አንስቶ ውድድር መታገድ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድባቸውም ነው ሰብሳቢው የገለጹት።

ክለቦች በመመሪያው ላይ ያላቸውን ቅሬታ ማቅረብ የሚችሉበት የአሠራር ሥርዓት መዘርጋቱንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ባህሩ ጥላሁን በበኩላቸው፤ በፕሪሚየር ሊጉ የሚሳተፉ ክለቦች ተጨዋቾችን ሲያስፈርሙ ማሟላት ያለባቸውን መስፈርቶች አስመልክቶ ገለፃ አድርገዋል።

ክለቦች አንድ ተጨዋች ሲያስፈርሙ ፌዴሬሽኑ ዝውውሩ የተሟላ መሆኑን ይፋ የሚያደርገው የሕይወትና የአደጋ ጊዜ ኢንሹራንስ፣ የሕክምና ሰርቲፊኬት፣ የልደት ሰርቲፊኬትና በፊት ከሚጫወትበት ክለብ መልቀቂያ(ክሊራንስ) ሲያሟሉ ብቻ ነው ብለዋል።

ፌዴሬሽኑ በመመሪያው አፈጻጸም ላይ ላይ ከሊጉ አክሲዮን ማኅበሩ ጋር በትብብር እንደሚሰራም አመልክተዋል።

መመሪያው ለተጨዋቾችና ለአሰልጣኞች በግል የሚከፈላቸው ክፍያ ላይ ገደብ እንደማያስቀምጥና ዋንኛ ትኩረቱ ዓመታዊ ጥቅል የክለቦች ክፍያ ጣሪያ እንደሆነና ከደመወዝና ጥቅማጥቅም ክፍያ ውጭ በሌሎች ወጪዎች ላይ ገደብ እንደማያስቀምጥ የአክሲዮን ማኅበሩ መረጃ ያመለክታል።

ማኅበሩ የተጨዋቾችና አሰልጣኞችን አጠቃላይ ዓመታዊ  ክፍያ የሚቆጣጠር ኮሚቴ ወደ ሥራ ማስገባቱ የሚታወስ ነው።

የ2017 የተጨዋቾች የዝውውር መስኮት ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን፤ እስከ መስከረም 26 2017 ዓ.ም ድረስ እንደሚቆይ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያሳያል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም