ቀጥታ፡

የመከላከያ ዋር ኮሌጅ የጀመራቸውን የለውጥ ሥራዎች በማስቀጠል አቅሙ የተገነባ ሠራዊት የመገንባት ሂደቱን ሊያጠናክር ይገባል 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2016(ኢዜአ)፦ የመከላከያ ዋር ኮሌጅ የጀመራቸውን የለውጥ ሥራዎች በማስቀጠል አቅሙ የተገነባ ሠራዊት የመገንባት ሂደቱን ሊያጠናክር ይገባል ሲሉ የመከላከያ መሃንዲስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ደስታ አብቼ አመለከቱ።  

የመከላከያ ዋር ኮሌጅ  በመደበኛና አጭር ኮርስ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በመጪው ቅዳሜ ያስመርቃል።     

ኮሌጁ የምረቃ በዓሉን ምክንያት በማድረግም በዛሬው ዕለት የተለያዩ መርሃ-ግብሮችን ያካሄደ ሲሆን፤  "የመከላከያ  ዋር ኮሌጅ  ከየት  ወዴት?" በሚል መሪ ኃሳብ  የኮሌጁ  ስኬቶች፣ የገጠሙ ፈተናዎችና  ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት ያደረገ የፓናል ውይይትም አካሂዷል።  

በመርሃ-ግብሩም የመከላከያ መሃንዲስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ደስታ አብቼ ጨምሮ  ጄኔራል መኮንኖችና ከፍተኛ መኮንኖች ተገኝተዋል።

ኮሌጁ የጀመራቸው የማስፋፊያ ፕሮጀክት የደረሱበት ደረጃና የኮሌጁ የሥራ እንቅስቃሴንም ሌተናል ጄኔራል ደስታ አብቼ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። 


 

ሌተናል ጄኔራል ደስታ አብቼ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ዘመናዊ ሠራዊት ለመገንባት ቀጣይነት ያለው ሥልጠና ተደራሽ ማድረግ የግድ ይላል።

በተለይም ከለውጡ ወዲህ ሠራዊቱን በሪፎርም የማጠናከር ጉዳይ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም አበረታች ውጤቶች እየተገኙ መሆኑን ጠቁመዋል።

መከላከያ ዋር ኮሌጅም የለውጡ ፍሬ ነው ያሉት ሌተናል ጄኔራል ደስታ፤ ኮሌጁ ተልዕኮውን፣ ዓላማና ግቡን ለማሳካት የጀመራቸውን የለውጥ ሥራዎች ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል። 

ኮሌጁ በሰው ኃይል፣ በሥርዓተ-ትምህርት እንዲሁም በመሠረተ-ልማት ራሱን ሊያጠናክር እንደሚገባም አጽንዖት ሰጥተዋል። 

የመከላከያ ዋር ኮሌጅ ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ቡልቲ ታደሰ በበኩላቸው፤ ዘመኑን  የዋጀ  ፕሮፌሽናል ሠራዊት መገንባት ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ ነው ብለዋል።


 

ለዚህ ደግሞ አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን የተገነዘበ የሠራዊት አመራር መገንባት ቁልፍ  ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል። 

ከዚህ  አኳያም  ኮሌጁ ስትራቴጂያዊ አመራር የማፍራት ሥራውን በትኩረት  እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ በረዥምና በአጫጭር ሥልጠናዎች በርካታ አመራር ማሰልጠን መቻሉን ተናግረዋል።  

ኮሌጁ ከመማር ማስተማር ሥራዎቹ ጎን ለጎንም የጥናትና ምርምር ሥራዎችም በስፋት እያከናወነ መሆኑንም ገልፀዋል። 

ኮሌጁ  የተመሠረተበትን ዓላማ በላቀ ደረጃ ለመፈጸም የለውጥ ሥራዎችን ተግባራዊ  ማድረጉን   ጠቁመው፤ በዚህም  ውጤታማ  መሆን መቻሉን አብራርተዋል።  

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ ጠቅላላ አገልግሎት የፋሲሊቲ ዳይሬክተር ኮሎኔል ዘካሪያስ ጥሩነህ በሰጡት አስተያየት፤ ኮሌጁ በመማር ማስተማሩ ሂደት የበለጠ ውጤታማ ለመሆን የመምህራንንና ስታፎችን አቅም መገንባት ላይ የበለጠ መሥራት አለበት ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደኅንነት ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፋና ገብረሰንበት በበኩላቸው፤ ኮሌጁ አገር በቀል እውቀቶችንና ልምድ ያላቸው የዘርፉ ባለሙያዎችን ይበልጥ  በመጠቀም ተቋሙን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።


 

ኮሌጁ የምረቃ በዓሉን ምክንያት በማድረግም የችግኝ ተከላና የደም ልገሳ መርሃ-ግብር አከናውኗል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም