የመዲናዋን መሰረተ ልማቶች በአግባቡ ለመጠበቅ የሚያስችል የደንብ ማስከበር ህግ ማሻሻያ ተደረገ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2016 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ደንብ ማሰከበር ባለስልጣን በመዲናዋ የተሰሩ የመሰረተ ልማት ስራዎችን ከጥፋት ለመጠበቅ የሚያስችል የደንብ ማስከበር ህግ ማሻሻያ ማድረጉን አስታወቀ፡፡ 

የደንብ ማስከበር ማሻሻያ ህጉን አስመልክተው የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣንና የአዲስ አበባ የፅዳት አስተዳዳር ኤጀንሲ በጋራ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የተሻሻለው ህግ በከተማዋ የለሙ ፓርኮች ፤ኮሪደሮች ፤መንገዶችና ተጓዳኝ ልማቶች የሚሰጡትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ለማስጠበቅ የሚያግዝ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የተገነቡት መሰረተ ልማቶች ለከተማዋ ጽዳትና ውበት መጠበቅ የላቀ አስተዋጽኦ ያላቸው መሆኑን ተከትሎ  ህጉን ማሻሻል ማስፈለጉ በዚሁ ወቅት ተብራርቷል።

የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹና ውብ ለማድረግ የኮሪደር ልማቶችን ጨምሮ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ነው።

በመዲናዋ የተገነቡትን የተለያዩ ፕሮጀክቶችና መሰረተ ልማቶች በአግባቡ ለመጠበቅ የህግ ማሻሻያዎች መደረጋቸው ሃብቶቹን ከጥፋት ለመታደግ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በዚህም ማንኛውም ሰው ያመነጨውን ደረቅ ቆሻሻ በግቢው ውስጥ በአግባቡ ያለመያዝና በአይነት ያለመለየት ፤ማዝረክረክ ፣ጤናና የአካባቢን ገጽታ በሚጎዳ መልኩ ማከማቸት 2ሺ ብር ያስቀጣል፡፡

ይህንኑ ተግባር ሲፈጽሙ የተገኙ ድርጅቶች ደግሞ እስከ 50 ሺህ  ብር የሚቀጡ መሆኑ ተገልጿል።

ደረቅ ቆሻሻን ከግቢው አውጥቶ ባልተፈቀደ ቦታ ላይ የጣለ ወይም ያስቀመጠ በግለሰብ ደረጃ 2 ሺህ ብር የሚቀጣ ሲሆን ከኢንዱስትሪ የወጣ ቆሻሻ ከሆነ  50 ሺህ ብር ያስቀጣል፡፡

ከጤና ተቋማት ወጥቶ ባልተፈቀደ ቦታ የተቀመጠ ወይም የተጣለ ቆሻሻ 30ሺህ ብር ከሌሎች  ድርጅቶች  የመነጨ ከሆነ ደግሞ 10 ሺህ እንደሚያስቀጣ በደንቡ ላይ ተቀምጧል፡፡ 

አሽከርካሪ ወይም ተሳፋሪ ከመኪና ወስጥ ሆኖ ማንኛውንም ዓይነት ደረቅ ቆሻሻ ውጭ ላይ ከጣለ 2 ሺ ብር እንደሚቀጣ ተደንግጓል፡፡ 

በተመሳሳይ እግረኞች ባልተፈቀደ ቦታ ወይም በፓርኮች፣ በአረንጓዴ ቦታ በኮሪደር መሰረተ ልማቶችና ሌሎች በህግ የተከለከሉ ቦታዎች ላይ የሚጥሏቸው የሲጋራ ቁራጮች ፣ሶፍትና መሰል የተለያዩ ማሸጊያ ወረቀቶችና የፍራፍሬ ተረፈ ምርቶች 2 ሺ ብር ያስቀጣሉ፡፡

በተደረገው የህግ ማሻሻያ መሰረት በህገ ወጥ መንገድ ፈሳሽና ደረቅ ቆሻሻ የሚጥሉ ሰዎች ወይም ድርጅቶች ዝቅተኛው 2 ሺህ ብር ከፍተኛው ደግሞ 100 ሺህ ብር ቅጣት እንደሚጣልባቸው ጠቁመዋል።


 

የአዲስ አበባ የፅዳት አስተዳዳር ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር እሸቱ ለማ በበኩላቸው፤ባለፉት ስድስት ዓመታት ከተማዋ ጽዱና ውብ እንዲሁም ለቱሪዝም የምትመች እንድትሆን በርካታ ስራዎች መከናወናቸው ገልጸዋል።

ከዚህ መከካል ትልቁና የከተማዋን ገጽታ መቀየረ በቻለው የኮሪደር ልማት የተለያዩ ፓርኮች፤ የህዝብ መዝናኛዎችና የተለያዩ የመሰረተ ልማት ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።

በህብረተሰቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ የተሰሩት የኮሪደር ልማቶቹ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉና በዘላቂነት ደህንነታቸው እንዲጠበቅ የህግ ከለላ ያስፈልጋል ብለዋል።

የቅጣት ማሻሻያ ከተደረገባቸው የደንብ መተላለፍ ህጎች መካከል በመንገድ ላይ መጸዳዳት፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ማዕከላት ውጭ ወይም መንገድ ዳር የሚጣሉ ተረፈ ምርቶች ፣ከመኖሪያ ቤትና ከድርጅት ግቢ ውጭ ያለውን አካባቢ አረንጓዴ አድርጎ አለመጠበቅ መኪና ባልተፈቀደ ቦታ ማጠብ ወይም ማሳጠብ  ይጠቀሳሉ፡፡

እንዲሁም በጫማ ጽዳትና ጥገና የተሰማሩ እንዲሁም በእረፍት ቀን ቅዳሜና እሁድ በመንገድ ንግድ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች እስከ አምስት ሜትር ያቆሸሹትን አካባቢ ካላጸዱ ቅጣት እንደሚጣልባቸው ተገልጿል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም