ህገ-ወጥ የቡና ንግድ እንቅስቃሴን ለመከላከል በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ የሚከናወነው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ህገ-ወጥ የቡና ንግድ እንቅስቃሴን ለመከላከል በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ የሚከናወነው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2016(ኢዜአ)፦ ህገ-ወጥ የቡና ንግድ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ የሚከናወነው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ዑመር ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ባለስልጣኑ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ጥራት ማስጠበቅ፣ ግብይትን ማዘመንና ህገ-ወጥ ንግድን መከላከልና መቆጣጠር ቅድሚያ በመስጠት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ናቸው፡፡
በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተካሄደው የኮንትሮባንድ ክትትል ስራ 180 ሚሊዮን ብር የሚገመት የቡና ምርት በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ለስራው ስኬታማነት መሰረታዊው ምክንያት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የምርት ማጓጓዝና የንግድ እንቅስቃሴ ተግባራዊ መደረጉ ነው ብለዋል፡፡
መተግበሪያው ከምርት ሽኝት ጣቢያ እስከ መዳረሻው ባሉ ሂደቶች ተገቢውን ክትትል በማካሄድ የኮንትሮባንድ ንግድን ለመቆጣጠር እያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የተገኘው ውጤት አበረታች በመሆኑ ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
ባለስልጣኑ ከተለያዩ የህግ አካላትና የቁጥጥር መስሪያ ቤቶች ጋር ግብረ ሀይል በማቋቋም በ2017 የምርት ዘመን ስራውን ለማስፋት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይም ሐሰተኛ ሰነድ በማሰራት ሕጋዊ አስመስለው የቁጥጥር ጣቢያዎችን ለማለፍ የሚሞክሩና ለውጭ ገበያ መቅረብ የሚገባውን ቡና ለሀገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብ የሚሰሩ አካላት እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡
ይህንን እኩይ ተግባር ለመግታት ከተለያዩ የህግ አስከባሪና ተቆጣጣሪ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ለአብነትም ባለፉት ሦስት ወራት ከፌደራል፣ ከኦሮሚያ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስና ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር ኮንትሮባንድ ቡና የጫኑ አስር ተሽከርካሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ተናግረዋል፡፡