ቀጥታ፡

ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን 550 ሄክታር መሬት ለኢንቨስትመንት ዝግጁ ማድረጉን ገለጸ

አዳማ፤ሀምሌ 17/2016(ኢዜአ):-ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን 550 ሄክታር መሬት ለኢንቨስትመንት ዝግጁ በማድረግ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን እያሟላ መሆኑን ገለጸ።

ልዩ ዞኑ ከ100 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶችን ለማስገባት ዝግጅቱን በማጠናቀቅ የተወሰኑትን እየተቀበለ መሆኑም ተመልክቷል።

ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን በሞጆና በአዳማ ከተሞች መካከል በ24,000 ሔክታር መሬት ላይ እየተገነባ ይገኛል።

ከጥቂት ወራት በፊትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑን ስራ አስጀምረዋል።

በወቅቱ በልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ ውስጥ ለሚገነባው ሉሜ ነጻ የንግድ ቀጠና የመሰረት ድንጋይ መቀመጡም የሚታወስ ነው።

ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ያከናወናቸው ተግባራትን አስመልክቶ ኢዜአ ከልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሞቱማ ተመስገን ጋር ቆይታ አድርጓል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ በዚህ ወቅት በልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ ውስጥ 550 ሄክታር መሬት ለባለሀብቶች ዝግጁ ተደርጎ መሰረተ ልማት የማሟላት ስራ እየተከናወነ ይገኛል።

ከመሰረተ ልማቶቹ መካከል በኢኮኖሚ ዞኑ ውስጥ 5 ነጥብ 1 ኪሎሜትር መንገድ መገንባቱን ገልጸው በቂ ውኃ ማቅረብ የሚችል መስመር መስከረም ላይ ስራ የሚጀምር መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም 230 ሜጋ ዋት ኃይል ማቅረብ የሚችል ንዑስ የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በቀጣይ ዓመት ጥር ወር ላይ ስራ እንደሚጀምርም አረጋግጠዋል።

''በተለይ ኤክስፖርትን የሚያስፋፉ እና ገቢ ምርቶችን የሚተኩ ኢንቨስትመንቶችን ለመቀበል ዝግጅት እያደረግን ነው'' ብለዋል።

እስካሁን ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑን ለማስተዋወቅ በተሰራው ስራ የተለያዩ ባለሃብቶች ወደ ዞኑ ገብተው ለመስራት ፍላጎት ማሳየታቸውን ገልጸዋል።

እነዚህ ባለሃብቶች ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ሲሆን ከፊሎቹ ወደ ልዩ ዞኑ በመግባት ሥራ  መጀመራቸውንም ተናግረዋል።

ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ ለስራ እድል ፈጠራ፣ ትልቅ የኢንቨስትመንት ካፒታልን ለመሳብ፣ የአገር ውስጥ ምርትን ለማሳደግ ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን አንስተዋል።

ከዚህም ባለፈ በአጠቃላይ እንደ አገር የኢንዱስትሪ ሽግግርን እውን ለማድረግ የተያዘውን ጉዞ የሚያሳካ ነው ብለዋል።

''ዞኑ ብዙ የኢንቨስትመንት ካፒታልን ወደ አገር ውስጥ ማስገባት የምንችልበት፣ ኤክስፖርት ምርቶችን የምናበረታታበት፣ ብዙ ገቢ የምናገኝበት ነው'' ሲሉም ገልጸዋል።

የፌዴራል መንግስት ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችን ማጠናከር የሚያስችሉ አዋጆችና የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ማውጣቱ ለስራቸው እጅግ ጠቀሜታ ያለው መሆኑንም አውስተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም