የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ በምድብ 1 ተደለደለ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ በምድብ 1 ተደለደለ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በ2024/25 የካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ሀገራት የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) ዞን ማጣሪያ በምድብ 1 ተደልድሏል።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የቻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ዕጣ ማውጣት ስነ ስርዓት ዛሬ በተቋሙ ዋና መቀመጫ ግብጽ ዋና ከተማ ካይሮ ላይ አከናውኗል።
ኢትዮጵያን በሴካፋ ዞን ወክሎ በማጣሪያ ውድድሩ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በምድብ 1 ከኬንያው ኬንያ ፖሊስ ቡሌትስ ፣ከሩዋንዳው ራዮን ስፖርትስ፣ ከደቡብ ሱዳኑ ዬ ጆይንት ስታርስና ከዛንዚባሩ ዋሪየር ኩዊንስ ጋር ተደልድሏል።
የታንዛኒያው ሲምባ ኩዊንስ፣ የብሩንዲው ፒቪፒ ቡዬንዚ፣ የዩጋንዳው ካዌምፔ ሙስሊምና የጅቡቲው ፋድ በምድብ 2 የተደለደሉ ክለቦች ናቸው።
የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ከነሐሴ 11 እስከ 29 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በማጣሪያ ውድድሩ የሚሳተፈው የዘንድሮው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ ነው።
ንግድ ባንክ በካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ሲሳተፍ የዘንድሮው ለአራተኛ ተከታታይ ዓመት ነው።
ክለቡ ከዚህ ቀደም ባደረጋቸው ሶስት ተሳትፎዎች በሁለቱ ፍጻሜ ደርሶ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። ባስመዘገባቸው ውጤቶች ለካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ማለፍ አልቻለም።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአራተኛ ተሳትፎው የማጣሪያ ውድድሩን ካሸነፈ ለመጀመሪያ ጊዜ በሻምፒዮንስ ሊጉ ይሳተፋል።
ካፍ በዘንድሮው የማጣሪያ ውድድር 38 ክለቦች በስድስት ዞኖች ተከፍለው ጨዋታቸውን እንደሚያደርጉ አስታውቋል።ክለቦቹ የካፍ የክለብ ላይሰንሲንግ መስፈርቶችን ማሟላታቸውንም ገልጿል።
በስድስቱ ዞኖች የሚያሸንፉ 6 ሀገራት፣ የወቅቱ የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ የደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሳንዳውንስና የውድድሩን የመጨረሻ ዙር የሚያዘጋጀው ሀገር ቡድን ጨምሮ 8 ክለቦች እ.አ.አ በ2025 ዋንጫውን ለማንሳት ይፋለማሉ።
የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የተጀመረው እ.አ.አ በ2020 ነው።
የደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሳንዳውንስ ሁለት ጊዜ ዋንጫውን ያነሳ ሲሆን የሞሮኮው ኤኤስ ፋር ራባት ውድድሩን አንድ ጊዜ አሸንፏል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በወንዶችም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ኢትዮጵያን ወክሎ እንደሚሳተፍ ይታወቃል።