ኢትዮጵያ እና ኩባ የሁለትዮሽ የፖለቲካ ምክክር ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ኩባ የሁለትዮሽ የፖለቲካ ምክክር ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ኩባ የሁለትዮሽ የፖለቲካ ምክክር ስምምነት መፈራረማቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከኩባ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢልዮ ኤድዋርዶ ሮድርጌዝ ፕርዶሞ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱም አምባሳደር ምስጋኑ ኩባ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ጠንካራ ግንኙነት አውስተው የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት በተለያዩ መስኮች ማጎልበት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የሁለትዮሽ ስምምነት የተካሄደባቸው የውሐ አስተዳደር፣ ትምህርት፣ የአየር ትራንስፖርት እና የንግድ ዘርፎች ላይ አጽንኦት የሰጡት ሚኒስትር ዴኤታው በህክምናና በስኳር ልማት ረገድ ያለውን ጠንካራ ግንኙነት አንስተዋል።
የኩባ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢልዮ ኤድዋርዶ ሮድርጌዝ ፕርዶሞ በኩላቸው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩባ ሀቫና ዳግም መከፈት ለሀገራቱ ግንኙነት መሳለጥ የሚጫወተውን ሚና አውስተዋል።
በውይይቱ ሁለቱም አካላት አለም አቀፍ ጫናዎችን በመቋቋም የጋራ ብልጽግናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ጉዳዮችን በትኩረት መስራት እንደሚገባ አረጋግጠዋል።
በውይይታቸው ወቅትም ኢትዮጵያ እና ኩባ የሁለትዮሽ የፖለቲካ ምክክር ስምምነት መፈራረማቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።