ወጣቱ ከአረንጓዴ አሻራ ልማት ጎን ለጎን ለዘላቂ ሰላም መስፈን ሊሰራ ይገባል -የብልጽግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቱ ከአረንጓዴ አሻራ ልማት ጎን ለጎን ለዘላቂ ሰላም መስፈን ሊሰራ ይገባል -የብልጽግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ
ደብረ ብርሀን ፤ሐምሌ 17/2016 (ኢዜአ)፦ ወጣቱ ከአረንጓዴ አሻራ ልማት ጎን ለጎን ለዘላቂ ሰላም መስፈን መስራት እንዳለበት የብልጽግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ አስገነዘበ።
በደብረ ብርሃን ከተማ "በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ "በሚል መሪ ሃሳብ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ የአረጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ተከናውኗል።
በብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ዋና ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ ወጣት ሰብለ በቀለ እንደገለፀችው መንግስት የዜጎችን ሰላም ለማስጠበቅና የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ነው።
የኢትዮጵያ የከፍታ ዘመን በጠንካራ መሰረት ላይ ለማቆም በመንግስት የተጀመሩ የልማትና የሰላም ስራዎች ላይ ተግቶ መስራት እንደሚገባ አስገንዝባለች።
በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ጎን ለጎን ለዘላቂ ሰላም መስፈን የውይይትና የምክክር ባህልን ማጎልበት እንደሚገባ ተናግራለች።
"በተያዘው የክረምት ወራት በመላ ሃገሪቱ በርካታ የሊጉ አባላት ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሰማርተው እየሰሩ ነው" ብላለች።
በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ወጣቶች ሊግ ሀላፊ ወጣት ተስፋሁን ተሰማ በበኩሉ "የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አንድነትን በማጠናከር ሁለተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ያግዛል" ብሏል።
በተያዘው ክረምት በክልሉ አባላትን በማስተባበር ችግኞችን በመትከል የአረጓዴ አሻራ መርሀ ግብርን የመደገፍ ስራ እየተከናወነ ነው" ብሏል።
በተጨማሪም 3 ሺህ የአረጋዊያንን መኖሪያ ቤቶችን ጥገናና አንድ ሺህ ቤቶች ደግሞ በአዲስ ለመስራት እንዲሁም 4 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አመልክቷል።
"ለአስር ሺህ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት እንደሚሰጥ ጠቅሶ " 20 ሺህ ደርዘን ደብተርና 5 ሺህ ፓኬት እስክሪብቶ በማሰባሰብ በአነስተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ቤተሰቦች ልጆች ድጋፍ ይደረጋል" ሲል አክሏል።
የክልሉን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ በምክክር ችግሮች እንዲፈቱ ውይይቶች እንደሚካሄዱም ተናግሯል።
"የተራቆቱ መሬቶችን በአረንጓዴ ለማልበስ የክረምት ችግኝ ተከላ በልዩ ትኩረት እየተከናወነ ነው" ያሉት ደግሞ የደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት ናቸው።
ወጣቶች በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ፥ በችግኝ ተከላ፣ የአቅመ ደካማ ቤቶችን በመጠገን፣ በደም ልገሳና በወንዝ ዳር ልማት በመሳተፍ ሀላፊነታቸውን እየተወጡ ነው ብለዋል።
በአንድነት ከተባበርን ሰላማችንን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን አረንጓዴ አሻራ ልማታችንን ለማስቀጠልና ከተረጅነት ለመላቀቅ አቅም አለን ብለዋል።
በከተማ አስተዳደሩ በተያዘው ክረምት ለደን፣ ለከተማ ውበትና ለምግብነት የሚያገለግሉ ችግኞች ተዘጋጅተው ተከላ እየተከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ከወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መካከል ተማሪ ሀይሌ ጋጭቶ በበኩሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፥ ስራን ከመልመድ ባሻገር ማህበራዊ መስተጋብሮችን እንድንወራረስ አግዞናል ብሏል።
"በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶችን እርስ በእርስ በመተዋወቅ ለሀገራዊ እሴት ግንባታ ተባብረን እንድንሰራ አግዞናል" ያለችው ደግሞ የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪ በጎ ፍቃደኛ ወጣት ቢታኒያ በትሩ ናት።
በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እየተሳተፉ ነው።