በመሬት ናዳው ለተጎዱ ወገኖች እና ቤተሰቦቻቸው መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
በመሬት ናዳው ለተጎዱ ወገኖች እና ቤተሰቦቻቸው መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2016(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን፣ ገዜ ጎፋ ወረዳ፣ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት ናዳ ለተጎዱ ወገኖችና ቤተሰቦቻቸው መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሰናይት ሰለሞን ገለጹ፡፡
የክልሉ መንግስት አመራርና ባለሙያዎችን ያካተተ ኮሚቴ በማቋቋም ችግሩ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸው የፌዴራልና የክልሉ ስራ አመራር ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር እና ሌሎችም አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
እስከ አሁን በተከናወነው ስራ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ሰብዊ ድጋፍ ማድረግን ጨምሮ በሕይወት የተረፉ የህክምና እርዳታ እንዲያገኙና ለጉዳት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎችን የማዘዋወር ተግባር መከናወኑን አስረድተዋል።
በተመሳሳይ ለአደጋው ተጋላጭ በሆኑ የክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የማሳሰብ ስራ እየተሰራ መሆኑን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የክልሉ መንግስት እያደረገ ካለው ድጋፍ በተጨማሪ ህብረተሰቡ፣ አጎራባች ዞኖችን ጨምሮ አጋር የልማት ድርጅቶች እያደረጉት ያለው ሰብአዊ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም የቢሮ ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡