በሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር የሀገርን ሰላም የሚያናጉና አብሮነትን የሚንዱ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ በቅንጅት ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
በሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር የሀገርን ሰላም የሚያናጉና አብሮነትን የሚንዱ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ በቅንጅት ይሰራል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2016(ኢዜአ)፦በሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር የሀገርን ሰላም የሚያናጉና አብሮነትን የሚንዱ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ በቅንጅት የሚሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳሬክተር መሀመድ ኢድሪስ ገለጹ።
በጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ የአገር ሰላምና አብሮነትን የሚሸረሽሩ አካላትን ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃን ለመከላከል ከፍትህ አካላት ጋር በቅንጅት የሚሰራባቸው ጉዳዮች ላይ እየመከረ ነው።
የባለስልጣኑ ዋና ዳሬክተር መሀመድ ኢድሪስ፤ በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የሀሳብ ነፃነት፣ ብዝሃነትና አካታችነት መፈጠሩን ገልጸዋል።
በዚህም ዜጎች በተለያዩ አማራጮች መረጃ የሚያገኙበትና ሀሳባቸውን በነጻነት የሚያንሸራሽሩበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።
በመሆኑም ይህንን መልካም እድል በአዋጅና በመመሪያ በመደገፍ ለዴሞክራሲና ለሀገር ግንባታ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የሀሰተኛ መረጃና ጥላቻ ንግግርን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ለማስፈጸም በሚደረገው ጥረት ሁሉም የሚጠበቅበትን ሚና ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
አዋጁን የማስፈጸም ጉዳይ የዜጎችን ሰላም የማስፈን ጉዳይ ነው ያሉት ዋና ዳሬክተሩ አዋጁን በትብብር በመፈጸም ሰላምን ማጽናት ተጠያቂነትን ማስፈን ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።
በሀሰተኛ መረጃ ስርጭት የሀገርን ሰላም የሚያናጉና አብሮነትን የሚንዱ አካላትን ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል።
የምክክር መድረኩ ሀሰተኛ መረጃና ጥላቻ ንግግርን ለመከላከል ከፍትህ አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሰራር በመፍጠር በጋራ ለመስራት የሚያግዝ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና መምሪያ ኃላፊ ሙሊሳ አብዲሳ፤ የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን መከላከል ካልተቻለ የሀገርና የህዝብ ህልውና አደጋ መሆኑን ገልጸዋል።
ከለውጡ በኋላ የመጣውን ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ባልተገባና ሀገርን በሚጎዳ መልኩ መጠቀም ተገቢነት የሌለውና በህግም ተጠያቂ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ የሀገርን ሰላምና አንድነት ለማናጋት በሚጥሩ አካላትን ፖሊስ በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራውን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በመድረኩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴምክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የፍትህ ሚኒስቴር፣ ሰላም ሚኒስቴር፣ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፓሊስ አመራሮችና ሌሎችም የፍትህ አካላት ተወካዮች ተገኝተዋል።