በግብርና ዘርፍ ጠቃሚ መረጃ ለማሰባሰብ ያለመ ጥናት ሊካሄድ ነው

አዳማ ፤ሐምሌ 17/2016 (ኢዜአ)፦በግብርና ዘርፍ መረጃ ለማሰባሰብ ያለመ ጥናት ሊያካሄድ መሆኑን የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ገለፀ።

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በሚያካሄደው ጥናት ለሚሳተፉ የግብርና ቆጠራ 2ኛ ዙር አሰልጣኞች ዛሬ ስልጠና መስጠት ጀምሯል።

ጥናቱ በግብርና ዘርፍ መዋቅራዊ ክትትልና በታችኛው የሴክተሩ ለውጥ ጠቃሚ መረጃ ለማሰባሰብ ያለመ ጥናት መሆኑም ተመላክቷል።

ለስልጠናው ተሳታፊዎች በ'ቨርቹዋል' መልዕክት ያስተላለፉት የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በከር ሻሌ፤ አገልግሎቱ ከ22 ዓመታት በኋላ 2ኛውን ዙር የግብርና ቆጠራ ለማካሄድ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

በተለይም የግብርና መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት በስነ-ምህዳር ጥበቃ፣ በድህነት ምጣኔ ቅነሳ፣ በመካከለኛ ዘመን ዕቅድ ትግበራ፣ በሌማት ትሩፋትና በከተማ ግብርና ዙሪያ ትኩረት ተደርጎ መረጃ ይሰበሰባል ብለዋል።


 

የጥናቱ ዓላማ የግብርና ዘርፍ መዋቅራዊ ለውጥና ውጤት ክትትል ለማድረግ በታችኛው የግብርና ዘርፍ ላይ የለውጥ ጠቋሚ መረጃዎችን ለማግኘት ነውም ብለዋል።

በተጨማሪም የግብርና ልማት ዕቅድ የተሻለ አፈፃፀም እንዲኖረው በሰብል ዓይነት ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትም የጥናት መረጃው የሚሰበሰብባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በሰብል የተሸፈነ መሬትና እየሰጠ ያለው ምርት፣ በእንስሳትና የእንስሳት ተዋፅዖ ልማት፣ በስነ-ምህዳር ጥበቃ ስራዎች ዙሪያ መረጃዎችን ለመሰብሰብ ያለመ ጥናት መሆኑንም አክለዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ የንግድ እርሻዎችና ልዩ እርሻዎች የጥናቱ አካል መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ጥናቱ የመኸር፣ የመስኖና የበልግ ልማትንም ያካትታል።

የጥናቱ የመረጃ አሰባሰብ ሂደቱ ለአንድ ዓመት የሚቆይ መሆኑን እና የጥናቱ ሰነዶችና ዝርዝር መርሃ ግብሮች ተዘጋጅተው የጥናቱ መጠይቆችም በስድስት ቋንቋዎች መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የግብርና ስታቲስቲክስ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ እስክንድር ተስፋዬ በበኩላቸው ዛሬ የተጀመረው 2ኛ ዙር የግብርና ቆጠራ የአሰልጣኞች ስልጠና ለተከታታይ 20 ቀናት የሚቆይ ነው።


 

አሰልጣኞቹ የስልጠና ቆይታቸውን አጠናቀው ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ 43 ሺህ ለሚሆኑ መረጃ ሰብሳቢዎች ስልጠና በመስጠት ከአዲሱ ዓመት ጀምሮ ወደ ስራ ያሰማራሉ ብለዋል።

ጥናቱ በሁሉም የኢትዮጵያ የገጠርና የከተማ ቀበሌዎች ላይ አርሶ አደሮችን፣ አርብቶ አደሮችንና ነዋሪዎችን በመሸፈን የሚካሄድ መሆኑንም ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም