ቀጥታ፡

ለፖሊስ ጥቆማ የሚደርስበት EFPapp መተግበሪያ በወንጀል መከላከልና የምርመራ ሂደትን በማሳለጥ ጉልህ አበርክቶ እያደረገ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2016(ኢዜአ)፦ ለፖሊስ ዜጎች ጥቆማ የሚያደርሱበት EFPapp ዲጅታል መተግበሪያ በወንጀል መከላከል የህብረተስቡን ተሳትፎ እያሳደገና የምርመራ ሂደትን በማሳለጥ ጉልህ አበርክቶ እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ገለጸ።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀልን ለመከላከያና የምርምራ ሂደቶችን ለማዘመን እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የፌዴራል ፖሊስ ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ጋር በመተባበር የበለጸገውን መተግበሪያ ባለፈው ግንቦት ወር መርቀው ስራ ማስጀመራቸው ይታወቃል።

ፖሊስ የዜጎችን ወንጀልን መከላከል ተሳትፎን  ለማሳደግ የአናሎግ ወደ ዲጂታል ስርዓት መሸጋገሩን ገልጸው፤ EFPapp ዜጎች ወንጀልን ለመከላከል በፎቶግራፍ፣ በቪዲዮ፣ በድምጽና በሰነድ ወይም ቀጥታ በመደወል መረጃ የሚሰጡበት መተግበሪያ መሆኑን አስረድተዋል።

በፌዴራል ፖሊስ የቴክኖሎጂ ማስፋፊያ መምሪያ ሃላፊ ኮማንደር ደምሴ ይልማ፤ መተግበሪያው በአዲስ አበባ ከተማ በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑ  ገልጸዋል።

በዚህም ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና ለአዲስ አበባ ፖሊስ ከ1 ሺህ 400 በላይ የህዝብ ጥቆማዎች ደርሰዋል ብለዋል።

በጥቆማዎቹ መሰረት መረጃዎች ተጣርተው እልባት እየተሰጣቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

የEFPapp ዲጅታል መተግበሪያ በወንጀል መከላከል የህብረተስቡን ተሳትፎ እያሳደገና የምርመራ ሂደትን በማሳለጥ ጉልህ አበርክቶ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ በሙከራ ደረጃ የተጀመረው መተግበሪያ በመላ ሀገሪቱ ስራ ላይ የሚውል መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በመላ ኢትዮጵያ አንድ አይነት አጭር የጥሪ ኮድ እንዲኖር ታስቦ 991 በሂደት ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።

አሰራሩም ዜጎች በቀላሉ ጥቆማ የሚሰጡበት አንድ አይነት ቁጥር እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም