ቀጥታ፡

በመጠለያ የነበረው አስቸጋሪ ጊዜ አብቅቶ ወደ ቀያችን ተመልሰን መደበኛ ህይወታችንን መምራት በመጀመራችን ተደስተናል- የአምባ ምድሪና የማይጠብሪ ከተማ ነዋሪዎች 

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 17/2016(ኢዜአ)፦በመጠለያ የነበረው አስቸጋሪ ጊዜ አብቅቶ ወደ ቀያችን ተመልሰን መደበኛ ህይወታችንን መምራት በመጀመራችን ተደስተናል ሲሉ የአምባ ምድሪና የማይጠብሪ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ። 

በሰሜን ምዕራብ እዝ የ501ኛ ኮር ምክትል አዛዥ ኮሎኔል ደረጀ ኩምሳ በበኩላቸው፤ ተፈናቅለው የቆዩ ዜጎች ወደ ቀያቸው ተመልሰው መደበኛ ህይወት እየመሩ መሆኑን ገልፀዋል። 

የአምባ ምድሪና የማይጠብሪ ከተማ ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው ተመልሰው ኑሯቸውን እየመሩና በልማት ሥራዎችም ላይ እየተሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል። 

ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ሻምበል ገብረየሱስ እና አትክልት ብርሃኔ፤በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ በሽሬ መጠለያ ጣቢያ ከሁለት ዓመት በላይ መቆየታቸውን ይናገራሉ።


 

በመጠለያ ጣብያ ህይወት አስቸጋሪ እንደነበር አንስተው፤አሁን ላይ ሰላም ተፈጥሮ ወደ ቀያቸው በመመለሳቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል። 

በሀገር መከላከያ ሠራዊት አስተባባሪነት በአማራና ትግራይ ክልሎች አመራሮችና አጠቃላይ የኅብረተሰቡ ትብብር ግጭትና ጦርነቱ አብቅቶ አሁን ላይ የሰላም አየር መኖሩን ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።

በዚህም ተፈናቅለው የቆዩ ሁሉ ወደ ቀያቸው እየተመለሱ መደበኛ ህይወትና ማኅበራዊ መስተጋብሮች ቀጥለዋል ብለዋል። 

በማይጠብሪ ከተማ የሚኖሩት አመልሰት በርሄም፤ የችግሩ ጊዜ አብቅቶ ወደ ሰላማዊ ህይወት ተመልሰን ለሌላ የደስታ ምዕራፍ ጀምረናል፤ ለዚህም የሀገር መከላከያ ሠራዊት ምስጋና ይገባዋል ብለዋል። 


 

ተፈናቅለው የቆዩ ዜጎች ወደ መኖሪያ ቀያቸው ሲመለሱ በየአካባቢው ማኅበረሰቡ ላደረገላቸው አቀባበልም ምስጋና አቅርበዋል። 

በዘላቂነት እስከሚቋቋሙ የመንግሥት አካላትና አጠቃላይ ሕብረተሰቡ የሚያደርገውን እገዛና ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ተመላሾቹ ጠይቀዋል። 

በሰሜን ምዕራብ እዝ የ501ኛ ኮር ምክትል አዛዥ ኮሎኔል ደረጀ ኩምሳ በበኩላቸው፤ ተፈናቅለው የቆዩ ዜጎች ወደ ቀያቸው ተመልሰው መደበኛ ህይወት እየመሩ መሆኑን ገልፀዋል። 


 

የሀገር መከላከያ ሠራዊትም የሰላምና መረጋጋት ሥራውን በአስተማማኝ መልኩ አስጠብቆ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል። 

በሰሜኑ ጦርነት ከሦስቱም የጠለምት ወረዳዎች ተፈናቅለው የነበሩ ከ10 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ መኖሪያ ቀያቸው መመለሳቸውን የሰሜን ምዕራብ እዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል መሠለ በለጠ መግለፃቸው ይታወሳል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም