ቀጥታ፡

በክረምት ወቅት የሚኖረው ከባድ ዝናብ በተፋሰስ አካባቢ ጉዳት እንዳያደርስ ከወዲሁ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል - የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2016(ኢዜአ)፦ በክረምት ወቅት የሚኖረውን ከባድ ዝናብ የጎርፍ አደጋ ስጋት ባለባቸው የተፋሰስ አካባቢዎችና በሌሎችም ጉዳት እንዳያደርስ ከወዲሁ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ።

የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ በአዋሽ፣ በአባይ፣ በባሮ አኮቦና በመሳሰሉት ተፋሰሶች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ትንበያው ያመለክታል።

የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከመጠን በላይና ጎርፍ የሚያስከትሉ ከባድ ዝናብ እንደሚኖራቸውም ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የጎርፍ አደጋ በተፋሰስ፣ በከተሞችና በረባዳማና ሸለቋማ ሥፍራ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጉዳት ሲያደርስ ይታወቃል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እነዚህን ችግሮች አስቀድሞ በመከላከልና በሚወሰደው የጥንቃቄ እርምጃ ጉዳቱን መቀነስ የሚያስችል ሥራ ቢሰራም በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መክሯል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የምታስተናግዳቸውን ወቅቶች በመለየት ትንበያ የሚሰጥ ሲሆን፤ በዘንድሮ የክረምት ወቅት ሊኖር የሚችለውን ትንበያ በግንቦት ወር ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተሰጥቷል።

ኢንስቲትዩቱ በፍጥነት እና በተደራጀ መልኩ መረጃ የሚያደርሱ ዘመናዊ የሚቲዎሮሎጂ መረጃ መሰብሰቢያ የመሠረተ-ልማት አውታሮችን የማስፋት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

የዘንድሮን ክረምት የሚወስነውን ዓለም አቀፍ የሚቲዎሮሎጂ ክስተት ከግምት ውስጥ በማስገባትም የላሊና ተጽዕኖ ሥር እንደሚሆን መተንበዩን ተናግረዋል።

ይህም በክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ከባድ ዝናብ እንደሚኖር ትንበያው ማመልከቱን ገልጸው፤ ሕብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም ነው ያሳሰቡት።

የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ በአዋሽ፣ በአባይ፣ በባሮ አኮቦና ሌሎች ተፋሰሶች አካባቢ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።

በከተሞች አካባቢ የውኃ ማስወገጃ ሥርዓቶችን በአግባቡ መቆጣጠርና መከታተል አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በክረምቱ ወቅት የሚኖረው ዝናብ በረባዳማና ሸለቋማ ሥፍራ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድር ጥንቃቄ መደረግ አለበትም ብለዋል።

በሌላ በኩል የአየር ሁኔታው ለግብርና እንቅስቃሴ ጉልህ ሚና ያለው በመሆኑ የሚኖረውን ዝናብ ምርታማነትን ለማሳደግ መጠቀም እንደሚገባም አቶ ፈጠነ አስገንዝበዋል።

በክረምቱ የሚኖረው ዝናብ ግድቦች የውኃ እጥረት ሳያጋጥማቸው ኃይል እንዲያመነጩና ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ውጤታማነት አስተዋፅዖ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም