ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም ለመፍጠር ምክክር አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው - ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው

አሶሳ፤ ሐምሌ 17/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም ለመፍጠር ምክክር አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው ገለጹ::

ኮሚሽኑ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለሀገራዊ ምክክር የሚሆን አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራ ዛሬ በይፋ ጀምሯል።

ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው የውይይት መድረኩን ሲከፍቱ እንዳሉት፤ በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች የሀሳብ ልዩነቶች ይታያሉ።

ልዩነቶችን መፍታት የሚያስችል የውይይት መድረክ ለማመቻቸት ኮሚሽኑ ሰፊ ጥረት እያደረገ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በእስካሁኑ ሂደት ስኬታማ የሚባሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።


 

የሀገሪቱን ሠላም ዘላቂ ለማድረግ የሀሳብ ልዩነታችንን ለመፍታት መምከር አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ሲሉም ኮሚሽነር ዘገየ ገልጸዋል።

የሀሳብ ልዩነት ግለሰቦችን ጫካ የሚያስገባ ሳይሆን የብዝሃነት ጌጥ መሆኑን መረዳት አለብን ያሉት ደግሞ ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ ናቸው።


 

የአጀንዳ ማሰባሰቡን ሥራ በተሳካ ሁኔታ በማድረግ በመከባበር እና በመደማመጥ ላይ የተመሠረተ ምክክር ማድረግ አለብን ብለዋል።

ለአንድ ሳምንት በሚካሄደው በዚሁ አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተወካዮች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም