ቀጥታ፡

ለአዲስ አበባ ከተማ ንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት እየተዘረጋ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2016(ኢዜአ)፦ ለአዲስ አበባ ከተማ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ለሚያቀርበው የለገጣፎ ለገዳዲ የውሃ ፕሮጀክት አስተማማኝ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት እየተዘረጋ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ዝርጋታው ከፍተኛ ጥራት ባላቸው ግብዓቶች የሚከናወን በመሆኑ ከዚህ በፊት የሚስተዋለውን የኤሌክትሪክ መቆራረጥ በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንስ እንደሆነም ገልጿል፡፡

ፕሮጀክቱ ግፊት የሚደርጉና የሚያጣሩ በአጠቃላይ 25 አዲስ ጉድጓዶችን የያዘ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 9 ነጥብ 6 ሜጋ ዋት ሃይል በቀን እንደሚጠቀም አስታውቋል፡፡


 

እስካሁን 79 ኪሎ ሜትር ያህሉ የተዘረጋ መሆኑንና 18 የተለያየ አቅም ያላቸው ትራንስፎርመሮች እና 1ሺህ 688 ከፍተኛ ጥራት ያላቸው የኮንክሪት ምሰሶዎች መተከላቸውን ጠቁሟል፡፡

በአሁን ሰዓት ለ16 የውሃ ጉድጓዶች የኤሌክትሪክ አቅርቦት ሥራው ተጠናቀው አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውንና ቀሪ ሥራዎች በጥቂት ጊዜ እንደሚጠናቀቁም አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም