በክልሉ በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ የተከናወኑ ሥራዎች የቱሪዝም ልማቱን እያሳደጉት ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ የተከናወኑ ሥራዎች የቱሪዝም ልማቱን እያሳደጉት ነው

ሐረር፤ ሐምሌ 17/2016 (ኢዜአ)፦በሐረሪ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ የተከናወኑ ሥራዎች የቱሪዝም ልማት እያደገ እንዲመጣ ማድረጋቸውን የክልሉ ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ ለኢዜአ እንደገለጹት በ2016 በጀት ዓመት የጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስን ጨምሮ በክልሉ ከተማና ገጠር ወረዳዎች ለሚገኙ ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርሶች የጥበቃና እንክብካቤ ሥራዎች ተሰርተዋል።
የጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስን ለነዋሪውና ለጎብኚዎች ሳቢ ለማድረግ በክልሉ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር 5ሺህ 600 ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገድ መገንባቱን ተናግረዋል።
ከቅርሱ መግቢያ በሮች አንዱ ለሆነው ሱጉጥ አጥ በሪ እንዲሁም የአውበርኸሌ አዋችና ሌሎች አድባራት፣ በጀጎል ውስጥ ለሚገኙ ባህላዊ ቤቶች እንዲሁም የፈረንሳዊው ባለ ቅኔ አርተር ራምቦ ማዕከል የዕድሳት ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
የሐረር ኢኮ ቱሪዝም ፓርክ የመጀመሪያ ምዕራፍ ሥራ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩንም አቶ ተወለዳ ተናግረዋል።
ከዚህም ባሻገር የሐረሪ ወንዶች ቆብ የአዕምሮ ንብረት ጥበቃ መለያ እውቅና እንዲያገኝ መደረጉን ነው የገለጹት።
በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው የሹዋኢሊድ ክብረ በዓል ዘንድሮም በርካታ የአገር ውስጥና የውጪ ጎብኚዎችና እንግዶች በተገኙበት በድምቀት መከበሩን አስታውሰዋል።
በክልሉ የሚከናወኑ የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ሥራዎች እንዲሁም ሸዋል ኢድን ጨምሮ የሚከናወኑ ክብረ በዓላት ማራኪና ጎብኚዎችን ለመሳብ አስተዋጾ እያደረጉ መምጣታቸውንም ገልጸዋል።
በተለይ የጎብኚዎችን ቁጥር በመጨመር የክልሉን የቱሪዝም ልማት ዘርፍ እያሳደጉ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
አቶ ተወለዳ እንዳሉት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በክልሉ ከ7ሺህ በላይ የውጪ ጎብኚዎች ወደ ሐረር በመምጣት የመስህብ ስፍራዎችን የተመለከቱ ሲሆን ይህም አምና ወደ ክልሉ ከመጡ ጎብኚዎች ጋር ሲነጻጸር ከ100 ፐርሰንት በላይ ብልጫ አለው።
ከ100ሺህ በላይ የአገር ውስጥ ጎብኚዎችም የክልሉን የተለያዩ የመስህብ ሥፍራዎች መጎብኘታቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ሥራው በተያዘው በጀት ዓመትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በሐረሪ ክልል የጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስ፣ በውስጡ ያሉ ጥንታዊ መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም አምስቱ መግቢያ በሮች እንዲሁም ባህላዊ የእደ ጥበብ ውጤቶች፣ የሐረሪ ሙዚየሞች፣ ሌሎች ታሪካዊ፣ ጥንታዊና ሃይማኖታዊ የመስህብ ስፍራዎች ይገኛሉ።