ቀጥታ፡

በፓሪስ ኦሊምፒክ የሚሳተፉ ስፖርተኞች የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት እና የቱሪዝም ሀብቶች ለአለም እንዲያስተዋውቁ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/2016(ኢዜአ)፦ በፓሪስ ኦሊምፒክ የሚሳተፉ ስፖርተኞች የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት እና የቱሪዝም ሀብቶች ለአለም እንዲያስተዋዉቁ የቱሪዝም ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።

ቱሪዝም ሚኒስቴር በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ለሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የሽኝት መርሐ ግብር አካሂዷል።

በሽኝት መርሐ ግብሩ ላይ የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በዚሁ ጊዜ ከሐምሌ 19 እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2016 ዓ.ም በሚካሄደው ውድድር ኢትዮጵያ በተለያዩ ስፖርቶች እንደምትሳተፍ ገልጸዋል።

በዚህም ውድድር የሚሳተፉ የኢትዮጵያ ልጆች አሸናፊነት በአለም ህዝብ ዘንድ የሚጠበቅ ነው።

ይህም ከትውልድ ትውለድ ሲተላለፍ ከመጣው የአሸናፊነት ታሪክ በመሆኑ ነው ብለዋል።

ይህንን መልካም ዕድል በመጠቀም የኢትዮጵያ መለያዎችንና መታወቂያዎችን ለአለም ህዝብ እንዲያስተዋውቁ ጠይቀዋል።

በተለይም የኢትዮጵያ ምድረ-ቀደምትነት የቡና፣ የአለም ትልቁ ወንዝ መገኛ፣ የአፍሪካ ነጻነት ምልክት መሆኑን በውድድሩ ወቅት እንዲያንፀባርቁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ለዚህም የሚሆን የተለያዩ የህትመት ስራዎች እና አልባሳት በቱሪዝም ሚንስቴር አማካኝነት እንደተዘጋጀ ተናግረዋል።

አትሌቶቻችን በሚያደርጓቸው ውድድሮች ካሸነፉ በኋላ ለ1 ደቂቃ ያህል በስታዲየሞች ውስጥ የሚከፈት የኢትዮጵያን ምድረ-ቀደምትነት የሚገልፅ ሙዚቃ እና ምስልም ለልዑክ ቡድኑ ተወካዮች አስረክበዋል።

አምባሳደር ናሲሴ አትሌቶች፣ የኦሊምፒክ ኮሚቴ እና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በፓሪስ ኦሊምፒክ የኢትዮጵያን ቱሪዝም ለማስተዋወቅ ከወዲሁ እያደረጉት ላለው ዝግጅት አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም