በመንገድ መሰረት ልማትና ደህንነት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመንገድ መሰረት ልማትና ደህንነት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/2016 (ኢዜአ):-ከተፈቀደው ክብደት በላይ በመጫን በመንገድ መሰረት ልማትና ደህንነት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ገለጸ።
በከፍተኛ የህዝብና የመንግስት ሃብት የተገነቡ የመንገድ መሰረተ ልማቶች የታለመላቸውን አገልግሎት ሳይሰጡ በተለያዩ ምክንያቶች ለብልሽት እየተዳረጉ መሆኑ ይታወቃል።
ለብልሽታቸው አንዱ መክንያት ደግሞ በተለይም የከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎች ከተፈቀደ ክብደት በላይ በመጫናቸው ነው።
በመሆኑም የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በ14 ጣቢያዎች የተጠናከረ የቁጥጥር ስራ እያከናወነ ይገኛል።
በመንገዶች አስተዳደር የመንገድ ሃብት ማኔጅመንት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አለማየሁ አየለ ለኢዜአ በሰጡት መግለጫ፤ በመንገድ መሰረት ልማትና ደህንነት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ከተፈቀደው ክብደት በላይ በመጫን ከንብረትም ባለፈ በህይወት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በጣቢያዎች ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በዘህ ረገድ በተለይም አሽከርካሪዎች ያለባቸውን ከፍተኛ ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል።
ማንኛውም አሽከርካሪ ከተፈቀደለት ክብደት በላይ ጭኖ ሲገኝ ትርፍ የሆነውን ጭነት በማራገፍ ለጥፋቱም የሚቀጣ መሆኑን ገልጸው ከሁለት ዓመት በፊት ተሻሽሎ የወጣው አዋጅም ይህንኑ የሚያጸና ነው ብለዋል።
ከክብደት በላይ በሚጭኑ አሽከርካሪዎች ላይ አስተዳደሩ ጥብቅ ቁጥጥር የሚያደርግ መሆኑን አረጋግጠው ችግሩን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ሁሉም እንዲያግዝ ጠይቀዋል።