ቀጥታ፡

የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አመራርና ሠራተኞች የአረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አመራርና ሠራተኞች ከአጋር ተቋማት ጋር በመሆን የአረንጓዴ አሻራቸውን በሞጆ-ሀዋሳ የፍጥነት መንገድ ዳርቻ አኑረዋል።

የዘንድሮው ሀገር አቀፍ  የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር "የምትተክል ሀገር የሚያፀና ትውልድ" በሚል መሪ ሃሳብ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በዚሁ መርሃ-ግብር የተለያዩ ተቋማት አሻራቸውን እያኖሩ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለትም የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አመራርና ሠራተኞች ከሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በመሆን በሞጆ-ሀዋሳ የፍጥነት መንገድ ዳርቻ አሻራቸውን አኑረዋል።

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዋና ስራ አስፈፃሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር)፤ የተቋሙ አመራርና ሰራተኞች የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ላይ ያላቸውን ተሳትፎ አጠናክረው ቀጥለዋል ብለዋል።


 

ከዚህ በፊት በሞጆ ዙሪያ ጠዴ ቀበሌ የተራቆተ መሬት ላይ ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ ለአካባቢው ማስረከብ መቻሉን አስታውሰው አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀዋል።

በዘንድሮው ዓመትም ከ30 ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ተግባራዊ እንቅስቃሴው ተጀምሯል ብለዋል።

የድርጅቱ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ወንድሙ ደንቡ፤ በተቋሙ ሰራተኞችና አጋር ተቋማት በሞጆ አከባቢ በርካታ ችግኞች እየተተከሉ አካባቢውም እየለማ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ሌላኛው የተቋሙ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ሲራጂ አብዱላ፤ በመርሃ ግብሩ ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን የመንከባከብ ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

በችግኝ ተከላው ተሳታፊ የሆኑ ሰራተኞችም በመርሃ ግብሩ ላይ በመሳተፋቸው መደሰታቸውን ገልጸው በቀጣይነትም ለመንከባከብ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የድርጅቱ አመራርና ሰራተኞች አሻራቸውን ያኖሩት ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ፣ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከጉምሩክ ኮሚሽን እና ከክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ጋር በጋራ በመሆን ነው።

በዘንድሮው ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም