ቀጥታ፡

የአፍሪካ አገራት የውኃማ አካላት ኃብቶች በዘላቂነት ለመጠቀም በዘርፉ ያላቸውን ትብብር ሊያጠናክሩ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/2016(ኢዜአ)፦የአፍሪካ አገራት የውኃና ውኃ አዘል ኃብቶችን በዘላቂነት ለመጠቀም የጋራ ትብብራቸውን ማጎልበት እንዳለባቸው የአፍሪካ ኅብረት አሳሰበ።

የአፍሪካ የውኃማ አካላት ሳምንት በአፍሪካ ኅብረት ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ዛሬ መከበር ጀምሯል።

የአፍሪካ ኅብረት የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ "ብሉ ኢኮኖሚ" እና ዘላቂ አከባቢ አየር ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ፤ አፍሪካ ያሏት የባህር፣ ውቅያኖስ፣ የተፈጥሮ ውኃና ሌሎች የውኃማ አካላት ኃብቶች  ለኢኮኖሚ እድገት፣ ለኢኮኖሚ ብዝኃነትና ለዘላቂ ልማት ጉልህ ፋይዳ እንዳላቸው ገልፀዋል።

አፍሪካ ኅብረት የውኃና ውኃ አዘል ኃብቶች (ብሉ ኢኮኖሚ) ዘላቂነትና የከባቢ አየር በጠበቀ መልኩ ለኢኮኖሚ ጥቅም እድገት ለማዋል የተለያዩ የአሠራር ማዕቀፎችን እየተገበረ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ኅብረቱ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2015 አንስቶ ለአሥር ዓመት የሚቆይ የአፍሪካ የባህርና ውቅያኖስ ፍኖተ-ካርታ እየተገበረ እንደሚገኝና የተቀናጀ የማሪታይም ስትራቴጂ ሥራ ላይ ማዋሉን ጠቅሰዋል።

በዚህም ኅብረቱ አባል አገራት የውኃማ አካላትን ጤና ባማከለ ሁኔታ እንዲጠቀሙ የግንዛቤ መፍጠር፣ የአቅም ግንባታና ተቋማዊ መዋቅርን የሚያጎለብቱ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዘርፋ ያለውን ቀጣናዊ ትብብርን ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። 

ብሉ ኢኮኖሚ አዲስ ጽንሰ-ኃሳብ በመሆኑ ለወጣቶችና ለተለያዩ ማኅበረሰብ ክፍሎች ግንዛቤ በመፍጠር አቅማቸውን መገንባት የተለየ ትኩረት እንደተሰጠውም አንስተዋል።


 

ብሉ ኢኮኖሚ የባህርና የውቅያኖስ ኃብቶችን ለኢኮኖሚ ልማትና እድገት መጠቀም ላይ ትኩረቱን ያደረገ መስክ ነው።

የውኃማ አካላትን ኃብቶች በዘላቂነት ለመጠቀም የጋራ ትብብር ያስፈልጋል ያሉት ኮሚሽነሯ፤ ለዚህም ሀገራትን ጨምሮ የዘርፉ ተዋንያን የተቀናጀ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የመንግሥታት ድርጅት የልማት መርኃ-ግብር የአፍሪካ ዳይሬክተር አሁና ኢዚያኮንዋ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት፤ አፍሪካ በብሉ ኢኮኖሚ ያላትን ሰፊ አቅም የአፍሪካን ብልፅግና ለማረጋገጥ መጠቀም እንደሚገባ ገልፀዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የብሉ ኢኮኖሚ በየዓመቱ 1 ነጥብ 5 ትሪሊየን ዶላር ገንዘብ የሚያንቀሳቅስ ዘርፍ መሆኑን ጠቁመዋል።

አፍሪካ ከዚህ ግዙፍ የኢኮኖሚ አቅም በመጠቀም አጠቃላይ አገራዊ የምርት መጠን (ጂዲፒ) ማሳደግ፣ በሚሊየኖች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠርና የምግብ ዋስትናዋን ማረጋገጥ እንደምትችል አመልክተዋል።

ዩኤንዲፒ አፍሪካ፤ አፍሪካ ያሏትን የውኃማ አካላት ኃብቶች በዘላቂነት በመጠቀም የኢኮኖሚ ትልሞቿን እንድታሳካ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። 

የኖርዌይ ዓለም አቀፍ ልማት ምክትል ሚኒስትር ቦርግ ሳንድካየር፤ የውኃማ አካላት ለአፍሪካ የምግብ አቅርቦትና የኢነርጂ ኃይል አማራጭን በማስፋት የኢኮኖሚ ጥቅሞችን ማስፋት የሚያስችላት ዘርፍ እንደሆነ ገልፀዋል።


 

የአየር ንብረት ለውጥ ለብሉ ኢኮኖሚ መስክ ትልቅ ፈተና መጋረጡን ጠቅሰው፤ ዘላቂነት ያለው የውኃ ኃብቶች አጠቃቀም ወሳኝ እንደሆነ አመልክተዋል።

ኖርዌይ የአፍሪካ የብሉ ኢኮኖሚ ዘርፍ  የፖሊሲ ማዕቀፍ ዝግጅትን ጨምሮ በዘርፉ ለበርካታ ዓመታት ድጋፍ እያደረገች መሆኑን ገልጸው፤ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። 

አፍሪካን ጨምሮ የዓለም አገራት በቀጣይ የፈረንጆች ዓመት በፈረንሳይ ኒስ ለሚካሄደው የተ.መ.ድ የውቅያኖስ ጉባዔ ከወዲሁ በጋራ አንድ አቋም በመያዝ ለዘላቂና ጤናማ የውኃማ አካላት ኃብቶች አጠቃቀም በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በዛሬው መርኃ-ግብር የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን አመራሮች፣ የኅብረቱ አባል አገራት ተወካዮች፣ የቀጣናዊ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዘርፉ ባለድርሻ አካላትና የልማት አጋሮች ተገኝተዋል።

በባህርና ውቅያኖስ ኃብቶች ላይ ግንዛቤ መፍጠርና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር የሚደረግበት የአፍሪካ የውኃማ አካላት ሳምንት እስከ ሐምሌ 18 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል።

ሳምንቱን በማስመልከት የሁለት ቀን አውደ-ጥናት ዛሬና ነገ የሚካሄድ ሲሆን፤ በተጨማሪም ሐምሌ 18 ቀን 2016 ዓ.ም የአፍሪካ የባህርና የውቅያኖስ ቀን ይከበራል።

የአፍሪካ የጠረፍና የደሴት አገራት በአጠቃላይ 13 ሚሊየን ስኩዌር ኪሎ ሜትር ገደማ የሚያካልል የውቅያኖስ ግዛት እንደሚሸፍኑ የአፍሪካ ኅብረት መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

 

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም