ቀጥታ፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ለስራ ዘመኑ ማስፈፀሚያ  ከ17 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አጸደቀ  

ታርጫ፤ሐምሌ 16/2016 (ኢዜአ)፡- የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት 6ኛ መደበኛ ጉባኤ ለ2017 የስራ ዘመን ማስፈፀሚያ የሚውል ከ17 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አጸደቀ።

የክልሉ ምክር ቤት የበጀት ፋይናንስ ኦዲት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ የኋላሸት በላይነህ እንደገለጹት፤ የፀደቀው በጀት ለክልል ማዕከል መስሪያ ቤቶች መደበኛና ካፒታል ወጪ፣ለዞኖች ጥቅል በጀት፣ለክልላዊ ፕሮግራሞች፣ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ነው።

ከፀደቀው በጀት ውስጥ   ከ10 ቢሊዮን 441 ሚሊዮን በላዩ በውስጥ አቅም የሚሸፈን መሆኑን አስታውቀዋል።

ቀሪው ደግሞ ከፌደራል መንግስት ድጎማና ከሌሎች የሚገኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።


 

የክልሉ ፋይናንስ እና ኢኮኖሚ  ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ወሰነች ቶማስ ፤ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ የክልሉ ወጪ 53 በመቶ በውስጥ ገቢ የሚሸፈን በመሆኑ ሁሉም መዋቅሮች በዚህ ላይ አተኩረው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል። 

በክልሉ የሚገኙ ዞኖች ያገኙትን ሀብት በሥራቸው ላሉ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ፍትሃዊ በሆነ መልክ በቀመር የማከፋፈል ስራን በፍጥነት ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው ተመልክቷል።


 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መሠተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር)፣ የክልሉ ኢኮኖሚ የሚያመነጨውን የገቢ አቅም አሟጦ በመሰብሰብ  የህዝቡን የልማት ጥያቄ መመለስ ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም