የስፖርትና የመዝናኛ ሥፍራዎች ወጣቶችን ከአልባሌ ቦታ እየታደጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የስፖርትና የመዝናኛ ሥፍራዎች ወጣቶችን ከአልባሌ ቦታ እየታደጉ ነው
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 16 ቀን 2016(ኢዜአ)፡- በአዲስ አበባ የተገነቡ የስፖርትና የመዝናኛ ሥፍራዎች ወጣቶችን ከአልባሌ ቦታ እየታደጉ መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣቶችና ታዳጊዎች ተናገሩ፡፡
መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ትውልድን የመቅረጽ ሥራ ነው፤ ለዚህም ልጆችና አዋቂዎች ትርፍ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉባቸው የስፖርትና የመዝናኛ ሥፍራዎች በስፋት እየተገነቡና እየታደሱ ለአገልግሎት እየበቁ ነው።
የተገነቡት አዳዲስ ፓርኮች የልጆች መጫወቻ ቦታዎችን እንዲሁም ወጣቶችና ታዳጊዎችን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው።
ኢዜአ በልደታ ክፍለ ከተማ በሚገኙ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችና በወዳጅነት ፓርክ የእረፍት ጊዜያቸውን ሲያሳልፉ የነበሩ ወጣቶችና አዳጊዎችን አነጋግሯል።
አስተያየት ሰጪዎቹ እንደሚሉት በክረምትና በእረፍት ጊዜ በከተማው በቂ የሆነ መዝናኛ ሥፍራ ባለመኖሩ፤ ያላቸውን ልዩ ተሰጥዖ ማውጣትና በቂ እረፍት ማድረግ ሳይችሉ ይቀሩ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአቅራቢያቸው የተገነባው የስፖርት ማዘውተሪያና መዝናኛ ሥፍራዎች ከሚያሳልፉት አልባሌ ቦታ እንደታደጋቸው ተናግረዋል።
በመዲናዋ ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ ከተሰሩ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ውስጥ በልደታ ክፍለ ከተማ የሚገኙት የብሪሞ እና ተስፋ የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከል ተጠቃሽ ናቸው።
በብሪሞ እና በተስፋ የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከላት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ካገኘናቸው ታዳጊዎች መካከል እዮሲያስ ኢብራሂም፣ ያፌት መኮንን እና ዘካሪያ መሀመድ ይገኙበታል።
ታዳጊዎቹ በመዲናዋ የስፖርት ማዕከላትን ለማዘመን የተሰሩ ተግባራቶች ጤናቸው ላይ ምንም ጉዳት በማያደርስ መልኩ የሚፈልጉትን ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ እንዳስቻላቸው ገልፀዋል።
ታዳጊዎቹ በተለይም አሁን ትምህርት የተዘጋበት የክረምት ወቅት በመሆኑ ጊዜያቸውን በስፖርታዊ እንቅስቃሴ እያሳለፉ መሆናቸው እራሳቸውን ከአልባሌ ቦታ እንዳይውሉ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።
ወጣት ሳራ ሳምሶን፣ ሀያት ረሺድ እና ሂክማ ሙሳ በመዲናዋ ተሰርተው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑ የመዝናኛ ሥፍራዎች ወጣቶች አዕምሯቸውን የሚያድሱበትን ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልፀዋል።
ወጣቶቹም እንደሚሉት በመዲናዋ በሚገኙ የመዝናኛ ሥፍራዎች በግልም ከጓደኞቻቸውም ጋር ሄዶ የመጎብኘት ልምድ እንዳላቸው ተናግረዋል።
እነሱም በመዲናዋ በሚገኙ የመዝናኛ ፓርኮች ሄደው ሲዝናኑ የደስተኛነት ስሜት እንደሚሰማቸውና ራሳቸውን ከመጥፎ አካባቢ እንዲያርቁ እንደሚያስችላቸው በመግለጽ መንግሥት በቱሪዝም ዘርፍ ላይ የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የአንድነት ፓርክ ከፍተኛ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ የሆኑት ጌታቸው በየነ በበኩላቸው፤ወቅቱ ትምህርት ቤቶች የሚዘገቡት እንደመሆኑ ወጣቶችና አዳጊዎች የእረፍት ጊዜያቸውን ሊጠቅማቸው በሚችሉ የመዝናኛ ሥፍራዎች ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ ጥሪ አቅርበዋል።
በተመሳሳይ የነገ ሀገር ተረካቢ ወጣቶች ባላቸው የትርፍ ጊዜ ነገ ራሳቸውን የተሻለ ደረጃ እንዳይደርሱ ከሚያደርጋቸው የመዝናኛ ሥፍራዎች ይልቅ ጤናቸውን በሚጠብቁ የመዝናኛ ሥፍራዎች ላይ እንዲያሳልፉም እንደዚሁ።