አየርላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የልማት ትብብር፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሚካኤል ማርቲን - ኢዜአ አማርኛ
አየርላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የልማት ትብብር፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሚካኤል ማርቲን
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/2016(ኢዜአ)፦ አየርላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የልማት ትብብር ለማጠናከር እንዲሁም የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማሳደግ እንደምትሰራ የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሚካኤል ማርቲን ተናገሩ።
የኢትዮጵያና የአየርላንድ የሁለትዮሽ ግንኙነት በርካታ ዓመታትን አስቆጥሯል።
ከዛሬ 30 ዓመታት በፊት አየርላንድ በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን መክፈቷም የሁለቱ አገራት ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጀመርን ያበሰረ ሲሆን ይህም የአገራቱ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር መሰረት መጣሉን ነው በሁለቱም ወገን የሚነሳው።
በቅርቡ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የመጡት የአየርላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የውጭ ጉዳይና መከላከያ ሚኒስትር የሆኑትን ሚካኤል ማርቲንም ላለፉት 30 ዓመታት ኢትዮጵያና አየርላንድ ፍሬያማ ግንኙነት እንደነበራቸው ለኢዜአ ገልጸዋል።
በእነዚህ ዓመታት አየርላንድና ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ውጤታማ የልማት ትብብር እንዳላቸው ገልጸው፤ በተለይም በልማታዊ ሴፍቲኔት፣ በትምህርትና በጤና ዘርፍ አበረታች አጋርነት መፍጠር መቻላቸውን ነው ያነሱት።
በቀጣይም በግብርና ዘርፍ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የምግብ ምርታማነትን ጨምሮ በሌሎች የልማት መስኮች ያሉ ትብብሮችን ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የሁለቱ አገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ወደ ሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ ቀጣይ የሁለቱ አገራት የቤት ሥራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም ላይ አየርላንድ በትኩረት እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያም እያካሄደች ያለው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለሁለቱ አገራት ብሎም ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ያላትን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት መጠናከር ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የሰሜኑን የአገሪቱ ክፍል መልሶ ለማቋቋምና ለመገንባት ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ለአምስት ዓመታት 20 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስፈልግ ገልጿል።
ይህንንም ተከትሎ አየርላንድ በቀጥታና በዓለም ባንክ በኩል እንዲሁም በአውሮፓ ኅብረት ማዕቀፍ ለሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ገቢራዊ ለማድረግ እየተሰራ ያለውን የሽግግር ፍትህ እንዲሁም አገራዊ ምክክር ከግብ ለማድረስ አየርላንድ ድጋፏን እንደምታጠናክርም ነው የገለጹት።
በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ና ከገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ጋር ውጤታማ የሆነ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
በአጠቃላይ፤ ጉብኝቱ ላለፉት ዓመታት በተለያዩ መስኮች ላይ የተመሰረተውን የአየርላንድና የኢትዮጵያን አጋርነት በቀጣይ ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል እድል የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
አየርላንድ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላምና ደኅንነት እንዲረጋገጥ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣውን ተጽዕኖ ለማቃለል ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ጋር በቅርበት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።