የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል እየተወሰዱ ያሉ የመፍትሔ አማራጮች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል እየተወሰዱ ያሉ የመፍትሔ አማራጮች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/2016(ኢዜአ)፦የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል እየተወሰዱ ያሉ የመፍትሔ አማራጮች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆኑን የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ተመራማሪና የኢኮኖሚ ባለሙያው ብርሃኑ ዓለሙ (ዶ/ር) ገለጹ።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በበኩሉ የዋጋ ግሽበትን አሁን ካለበትም ለማውረድ የሚያስችሉ የመፍትሄ አማራጮች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ገልጿል።
የሰው ልጆችን የኑሮ ሁኔታ እየፈተነ ያለውን የዋጋ ግሽበት ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት ሁሉን አቀፍ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ይታመናል።
በኢኮኖሚ ውስጥ ከሚፈለገው በላይ የገንዘብ መሠራጨት፣ የፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣምና ሌሎችም ለዋጋ ግሽበት ምክንያቶች መሆናቸውን የምጣኔ ኃብት ምሁራን ይገልጻሉ።
በኢትዮጵያም ፈተና ሆኖ የቀጠለውን የዋጋ ግሽበት ለመከላከል በመንግሥት የተለያዩ የመፍትሔ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ተመራማሪና የኢኮኖሚ ባለሙያው ብርሃኑ ዓለሙ (ዶ/ር)፤ የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል የተለያዩ የመፍትሔ እርምጃዎች አስፈላጊ መሆናቸውን አብራርተዋል።
የወለድ መጠንን በመጨመርና የዜጎችን የቁጠባ ባህልን በማዳበር በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ገንዘብ ወደ ባንክ እንዲሰበሰብ ማድረግ እንደ አንድ መፍትሔ የሚወሰድ መሆኑን አስረድተዋል።
የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ መሸጥ ገንዘብን ከኢኮኖሚው መሰብሰብ ሌላው አማራጭ ሲሆን፤ የብድር ወለድንም ከፍ በማድረግ የገንዘብ ተገቢ ያልሆነ ሥርጭትን መግታት ይቻላል ብለዋል።
በመሆኑም በእነዚህና ሌሎችም ተያያዥ የመፍትሔ አማራጮች የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል መንግሥት እያደረገ ያለው ጥረት ተጨባጭ ውጤት እየታየበት መሆኑን የስታትስቲክ መረጃዎችን ጠቅሰው አብራርተዋል።
በምግብና ምግብ ነክ ባልሆኑ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ግሽበቱ ባለፈው ዓመት ከነበረበት ቅናሽ ማሳየቱን እንዲሁም በ2016 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ 23 በመቶ የነበረው የዋጋ ግሽበት ወደ 19 ነጥብ 9 በመቶ ዝቅ ማለቱን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
የምርት ፍላጎትና አቅርቦትን ለማመጣጠን የሌማት ትሩፋትን ጨምሮ ሌሎችም የግብርና ልማት ሥራዎችም የመፍትሔው አካል ስለመሆናቸው አስረድተዋል።
በሸማቾች ማኅበራት በኩል የተለያዩ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ መቅረባቸውም ለዋጋ ግሽበት መቀነስ በመፍትሔነት የሚጠቀስ መሆኑን ዶክተር ብርሃኑ ገልፀዋል።
የንጋት በንፋስ ስልክ ሸማቾች ዩኒየን የቦርድ ሰብሳቢ አቶ መክብብ ምናሴ፤ ዩኒየኑ ከገበሬዎች ሕብረት ሥራ ማኅበራት ጋር በገባው ውል መሠረት የግብርና ምርቶችን በመሠረታዊ ማኅበራት በኩል ለኅብረተሰቡ እያቀረበ ስለመሆኑ አንስተዋል።
የብርሃን ለሕዝብ ሸማቾች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ተወካይ መቶ አለቃ ባዬ ደርበው፤ የቅዳሜና እሁድ ገበያን ጨምሮ በማኅበሩ ምርት በቅናሽ ዋጋ እያቀረበ መሆኑን ገልፀዋል።
በቀጣይም የተለያዩ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በብዛትና በስፋት የማቅረቡ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፤ እንደ ሀገር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተሰሩ ሥራዎች የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርጓል ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተጀመረው የሌማት ትሩፋት እና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትም ምርታማነትን በማሳደግ ያመጣውን ተጨባጭ ውጤት አንስተዋል።
በቀጣይም እነዚህን እና ሌሎች የግብርና ልማት ሥራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል የዋጋ ግሽበትን አሁን ካለበትም ለማውረድ ይሰራል ብለዋል።