የአፍሪካ የውሃማ አካላት ሳምንት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ የውሃማ አካላት ሳምንት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/2016(ኢዜአ)፦ በባህርና ውቅያኖስ ሀብቶች ላይ ግንዛቤ መፍጠር አላማው ያደረገ የአፍሪካ የውሃማ አካላት ሳምንት (ብሉ ኢኮኖሚ) ዛሬ በአፍሪካ ሕብረት ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ተጀምሯል።
“የአፍሪካን የብሉ ኢኮኖሚ ሕዳሴ እውን ማድረግ” በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን የአፍሪካ የውሃማ አካላት ሳምንት ያዘጋጁት የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን፣ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) እና አጋር አካላት ናቸው።
የአፍሪካ የውሃማ አካላት ሳምንት የተመለከተ አውደ ጥናት በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በአውደ ጥናቱ ላይ የአፍሪካ ሕብረት የግብርና፣ገጠር ልማት፣ 'ብሉ ኢኮኖሚ' እና ዘላቂ ከባቢ አየር ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ፣ የኖርዌይ የዓለም አቀፍ ልማት ምክትል ሚኒስትር ቦርግ ሳንድካየር፣ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን አመራሮች፣ የሕብረቱ አባል ሀገራት ተወካዮች፣ የዘርፉ ተዋንያንና አጋር አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።
ሳምንቱ የባህርና ውቅያኖስ ሀብቶች ''ብሉ ኢኮኖሚ'' ፅንሰ ሀሳብ ላይ ሁሉን አቀፍ መረዳት መፍጠር እንዲሁም ያላቸውን ጠቀሜታዎችና ፈተናዎች የማስገንዘብ አላማ ያለው ነው።
የተለያዩ የዘርፉ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር በብሉ ኢኮኖሚ ያሉ እድሎች ላይ በመምከር የጋራ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል ትርጉም ያለው ትብብርን ማጠናከር የሚያስችል ምቹ መደላድልን ይፈጥራል ተብሏል።
ፖሊሲ አውጪዎች በብሉ ኢኮኖሚ ላይ አዳዲስ የፖሊሲ ማዕቀፎችን ማዘጋጀትና በአፍሪካ የዘርፉን ኢኮኖሚ መደገፍ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ምክክርና የልምድ ልውውጥ እንደሚያደርጉ ተገልጿል።
የአፍሪካ ሴቶችና ወጣቶች በብሉ ኢኮኖሚ ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ በማሳደግና በነሱ የሚመሩ የኢኮኖሚ ማዕቀፎችና የፈጠራ ሀሳቦችን መንደፍ ላይ ውይይት እንደሚደረግም ተመላክቷል።
የብሉ ኢኮኖሚ አማራጮች ፣ ዓለም አቀፍ የውቅያኖስ ኢኮኖሚ፣ ቱሪዝም፣ የውሃ ሀብቶች ጥበቃና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲሁም ወጣቶችን ማብቃት ውይይት የሚደረግባቸው ርዕሰ ጉዳዮች እንደሆኑ ኢዜአ ከአፍሪካ ሕብረት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
የአፍሪካ ውሃ አካላት ሳምንት እስከ ሐምሌ 18 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል።
የአፍሪካ የባህርና የውቅያኖስ ቀን ከነገ በስቲያ ይከበራል።