አትሌቶች ወደ ፓሪስ ይዛችሁ የምትሄዱት ኢትዮጵያን በመሆኑ ለስኬት መትጋት ይጠበቅባችኋል- ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
አትሌቶች ወደ ፓሪስ ይዛችሁ የምትሄዱት ኢትዮጵያን በመሆኑ ለስኬት መትጋት ይጠበቅባችኋል- ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 15/2016(ኢዜአ)፦አትሌቶች በፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከምንም በላይ ኢትዮጵያን በማስቀደም ሀገራቸውን ስኬታማ ለማድረግ መትጋት እንዳለባቸው ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።
በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ለሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የሽኝት መርሐ በብሔራዊ ቤተ መንግስት እየተካሄደ ይገኛል።
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት፤ አትሌቶች በተለያዩ የዓለም መድረኮች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
በፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይም ኢትዮጵያ ብዙ ሜዳሊያዎችን እንደምታመጣ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡
አትሌቶች ኢትዮጵያን በማስቀደም በጠንካራ የቡድን መንፈስና ትብብር ሀገራቸውን ውጤታማ ለማድረግ መስራት እንደሚኖርባቸውም ተናግረዋል።
ማንም ኢትዮጵያዊ በሀገሩ ክብር አይደራደርም፤ ኢትዮጵያዊነት በጋራ የመቆም አቅምና መንፈስን የሚያጎናጽፍ ማንነት ነው ብለዋል።
አትሌቶች ሀገርን ከማስጠራት ጎን ለጎን በስፖርታዊ ጨዋነት ውድድራቸውን እንዲያደርጉም ነው ጥሪ ያቀረቡት።
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አስረክበዋል።
33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከሐምሌ 19 እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2016 ዓ.ም በፓሪስ ይካሄዳል።
በውድድሩ ላይ ከ206 ሀገራት የተወጣጡ (በዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ጥላ ስር የሚወዳደሩ ገለልተኛ አትሌቶችና የኦሊምፒክ የስደተኞች ቡድን ጨምሮ) 10 ሺህ 714 ስፖርተኞች በ32 የስፖርት ዓይነቶች ይሳተፋሉ።
ኢትዮጵያም በአትሌቲክስ፣ ውሃ ዋናና ቦክስ በ39 ስፖርተኞች ትሳተፋለች።