ኢትዮጵያ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የምታደርገውን ጥረት የፋይናንስ ተቋማት ሊደግፉት ይገባል - አቶ አህመድ ሽዴ

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 15/2016(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ለምታከናውነው አካታች የመሰረተ ልማት ግንባታ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ተገቢ ድጋፍ ሊደረግላት እንደሚገባ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ገለጹ፡፡

እ.አ.አ ከሰኔ 30 እስከ ሐምሌ 3 ቀን 2025 በስፔን ለሚካሄደው 4ኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ ቅድመ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡


 

ጉባኤው እ.አ.አ በ2015 በአዲስ አበባ በተዘጋጀው ሶስተኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ኮንፍረንስ በጸደቀው የውሳኔ ሀሳብ (Addis Ababa Action Agenda, Resolution 69/313) እና በ2030 የዘላቂ ልማት ግቦች ትግበራ ላይ የሚመክር ነው፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በዚህ ጉባኤ ላይ እንዳሉት፤ በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ሳቢያ ዓለም ባልተረጋጋ የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ ይገኛል ብለዋል። 

በዚህም ኢትዮጵያን ጨምሮ ታዳጊ ሀገራት በዓለም ኢ-ፍትኃዊ የፋይናንስ ሥርዓት ምክንያት ችግር እየገጠማቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የ2015ን የአዲስ አበባ የውሳኔ ሀሳብ እና አጀንዳ 2030ን ለማሳካት በርካታ ሥራዎችን አከናውናለች ብለዋል፡፡

ከ2015 በኋላ የባንኮችን ቁጥር በማሳደግ የዘርፉን አገልግሎት ማዘመን፣ በዲጅታል የፋይናንስ ስርዓት የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚዎችን ቁጥር በ2019 ከነበረበት 4 ነጥብ 9 ሚሊዬን በ2023 ወደ 27 ነጥብ 9 ሚሊዬን ማሳደግ እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡

የታክስ አስተዳደር ስርዓቱን በማሻሻል ባለፉት ሶስት ተከታታይ  ዓመታት የሚሰበሰበውን ገቢ በአማካይ በ24 ነጥብ 9 በመቶ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በጤና፣ ትምህርት፣ ንፁህ መጠጥ ውሃና መሰል መሰረተ ልማቶች ላይ በትኩረት እንደምትሰራ ገልጸው፤ አጀንዳዎችን ሙሉ በሙሉ ለማሳካት ግን የሁሉንም ትብብር እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ የአዲስ አበባን የውሳኔ ሀሳብና አጀንዳ 2030ን ለማሳካት የምታደርገውን ጥረት ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በቁርጠኝነት ሊደግፉት ይገባል ብለዋል፡፡


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ በበኩላቸው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የገጠመውን የፋይናንስ ችግር ለመፍታት ዓለም አቀፍ ጉባኤ መዘጋጀቱ የላቀ ሚና አለው ብለዋል። 

የአዲስ አበባን የውሳኔ ሀሳብ እና አጀንዳ 2030ን ለማሳካት እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና ዓለም ባንክ አይነት ተቋማት ድጋፋቸውን በችሮታ ሳይሆን በቁርጠኝነት ሊያቀርቡ ይገባል ብለዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት አካታች ሪፎርም ሊያደርጉ እንደሚገባ ገልጸው፣ ሕገ-ወጥ የፋይናንስ ዝውውርን በጋራ መከላከል እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

ዓለም ፍትሀዊ የፋይናንስ ስርጭት ችግር እንጂ የገንዘብ እጥረት ስለሌለበት የታዳጊ ሀገራትን የእዳ ጫና በመቀነስ ዘላቂ ልማት ላይ እንዲያተኩሩም ጠይቀዋል፡፡


 

የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በዓለም ላይ በጂኦ ፖለቲካ ልዩነት ላይ የተመሰረተ ኢ-ፍትሐዊ የፋይናንስ ፍሰት ችግር መፈጠሩን አንስተዋል።

በመሆኑም በስፔን የሚካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ንግድና ኢንቨስትመንትን በማጠናከር የተሳለጠ የፋይናንስ ስርዓት ለመዘርጋት የጎላ አበርክቶ ይኖረዋል ብለዋል።

በትብብር በመስራት የፋይናንስ ስርዓቱን በማዘመን እኩልነትና ፍትሀዊነት የሚታይበት የፋይናንስ ስርአት መዘርጋት እንችላለን ሲሉም ተናግረዋል።


 

የመንግስታቱ ድርጅት ምክትል ዋና ጸሀፊ አሚና መሀመድ፤ በፋይናንስ ፍሰቱ ላይ ፈተናዎች ቢበዙም ከ2015 ወዲህ ተስፋ ሰጭ እንቅስቃሴዎች ታይተዋል ብለዋል፡፡

በዘላቂ የልማት ግቦች ላይ ኢንቨስት የማደረግ ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው ከሚያስፈልገው አንፃር በቂ ስላልሆነ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም