ቀጥታ፡

በጎፋ ዞን በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ የ20 ሰዎች ሕይወት አለፈ

አርባ ምንጭ ፤ሐምሌ 15/2016(ኢዜአ)፡-በጎፋ ዞን በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ የ20 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ ለኢዜአ እንደገለጹት አደጋው ዛሬ ጠዋት ንጋት ላይ የተከሰተው በዞኑ ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ቀበሌ ሲሆን በአደጋውም የ20 ሰዎች ህይወት አልፏል።

የአደጋው መንስኤ ትናንት ሌሊት ለአምስት ሰዓታት በጣለው ከፍተኛ ዝናብ በቀበሌው ተራራማ ስፍራ በሚገኝ መንደር ላይ በተከሰተ የመሬት ናዳ መሆኑን ተናግረዋል።

ዋና አስተዳዳሪው እንደገለጹት በአደጋው የአንድ ቤተሰብ አምስት አባላት ሙሉ ለሙሉ ሕይወታቸው አልፏል።

እስካአሁንም የ20 ሰዎች አስከሬን መገኘቱን የገለጹት አስተዳዳሪው የሟቾች ቁጥር ከእዚህም በላይ ሊጨምር እንደሚችል ገልጸዋል። 

ሕይወታቸው ካለፈ ሰዎች መካከል በአፈር የተዳፈኑትን ለማውጣት ርብርብ ሲያደርጉ የነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎችም ጭምር እንዳሉ ጠቁመዋል።

ከአደጋው አምስት ሰዎች በሕይወት መትረፋቸውን ኢንጂነር ዳግማዊ ጠቁመው፣ በአፈር ውስጥ የተቀበሩትን ለማውጣት ፍለጋው አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም