የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በጣልያን ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች እና በቤት ግንባታ ዘርፍ ከተሰማሩ ድርጅቶች ጋር ተወያየ - ኢዜአ አማርኛ
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በጣልያን ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች እና በቤት ግንባታ ዘርፍ ከተሰማሩ ድርጅቶች ጋር ተወያየ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 15/2016(ኢዜአ)፦ በፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የተመራው ልዑክ በጣሊያን ከሚኖሩ ዳያስፖራዎች እና የመኖሪያ ቤት ግንባታ ቴክኖሎጂ ድርጅቶች ጋር ተወያየ፡፡
ውይይቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በሮም የሚገኘው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ኤምባሲ እንዳመቻቹት ተገልጿል፡፡
በውይይቱ ኮርፖሬሽኑ በጣሊያን ዋና ከተማ ሮም እና ሚላን ከተማ ከሚኖሩ ዳያስፖራዎች እና በጣሊያን ከሚገኙ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ቴክኖሎጂ ባለቤቶች ጋር ሰፊ ምክክር ማድረጉም ተመላክቷል፡፡
በውይይቱ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎችን ታሳቢ ያደረገ የመኖሪያ ቤት ግንባታ መርሀ ግብር ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችለውን ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡
በተመሳሳይ በጣሊያን ከሚገኙ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ቴክኖሎጂ ባለቤት ጋር አብሮ ለመስራት ስምምት ላይ በመደረሱ ኮርፖሬሽኑ ተግባራዊ በሚያደርጋቸው መርሀ ግብሮች ላይ አዲስ የግንባታ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ለማዋልም ስምምነት ላይ መደረሱ ተጠቁሟል፡፡
በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵውያን በሀገራቸው ሀብትና ንብረት እንዲኖራቸው ብሎም በሀገራቸው ልማትና እድገት የራሳቸውን ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እነርሱን ታሳቢ ያደረገ የቤት ልማት መርሀ ግብር ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅት መጠናቀቁን የኮርፖርሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈደጻሚ አቶ ረሻድ ከማል መግለጻቸውም እንዲሁ፡፡
በሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ደሚቱ ሐምቢሳም የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዳያስፖራውን የሚያሳተፍ የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ለመጀመር መዘጋጀቱ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከሀገራቸው ልማት እንቅስቀሴ ጋር እንዲተሳሰሩ የበኩሉን ሚና ስለሚጫወት ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ኮርፖሬሽኑ የሚተግበራቸው ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ያደረጉ መርሀ ግብሮች እንዳሉት አቶ ረሻድ ከማል መጠቆማቸውም ተገልጿል፡፡
መርሀ ግብሮችን ተግባራዊ ለማድረግ የፋይናንስ ማፈላለግ እና የግንባታ ቴክኖሎጂ አማራጮች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ከህግ-ማዕቀፍ በተጨማሪም የዲዛይን፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ስለሚኖረው ቁጠባና የብድር አገልግሎቶችና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር የተገናኙ የቅድመ-ዝግጅት ስራዎች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዳያስፖራ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ለማ ዋቄዮ በበኩላቸው በፌደራል ቤቶች ኮርፓሬሽን ለሚጀመረው የዳያስፖራ የቤቶች ልማት ባንኩ ብድር ማቅረብ እንደሚችልም ገልጸዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ዳያስፖራዎች ኮርፖሬሽኑ እያስመዘገበ ባለው ውጤት ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው የቤት ልማት መርሀ ግብሩ ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን መግለጻቸውን ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።